
AMN-ግንቦት 15/2017 ዓ.ም
አምስተኛው ዙር የአሜሪካ እና ኢራን የኒውክሌር ድርድር በዛሬው ዕለት በጣሊያን ሮም እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ ፤ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣርያ ማምረት እንዳትችል ዩራኒየም ማበልጸጓን ጨርሶ እንድታቆም ትፈልጋለች፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለዚህ የአሜሪካ ፍላጎት በሰጡት ምላሽ ፤ ዩራኒየም ጨርሶ አታልሙ ማለት “ምንም አይነት ስምምነት የለንም’’ ከማለት ይቆጠራል ብለዋል፡፡
አራግቺ በኤክስ የማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው በስተላለፉት መልዕክት ፤ “የስምምነት መንገድን መፈለግ የሮኬት ሳይንስ አይደለም” በማለት ፍላጎቶች በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊቻቻሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ትራምፕ ከሰሞኑ በባሕረ ሰላጤው ሀገራት በነበራቸው ጉብኝት ፤ ሀገራቱ በኢራን የኒውክሌር መርሐ-ግብር ላይ ከስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሠላማዊ ተግባራት የሚውል ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ሀገራቱ በጉዳዩ ላይ ለአምስተኛ ዙር የሚያደርጉት ድርድር ዛሬ በጣሊያን ሮም እንደሚካሄድም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡