AMN – ጥር 11/2017 ዓ.ም
የበሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተላከ መልዕክት ለዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ለኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አድርሰዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁለቱ መሪዎች መልካም ጉርብትና እና ቀጣናዊ ትብበር እንዲጠናከር ለተጫወቱት በጎ ሚና እንዲሁም ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጠያቄ ላሳዩት ቀናዒነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያላቸውን አድናቆት ገልጸውላቸዋል።
ፕሬዚዳንቶቹም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር እንዲሁም በራሷ አቅም በሶማሊያ እና በሌሎችም ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ያበረከተችውን አይተኬ ሚና በማውሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመጫወት ለይ ያሉትን ጉልህ ሚና ማድነቃቸውን እና በቀጣይም በሶማሊያ ሰላም እና ሽብርተኝነትን በማዋጋት ረገድ የሚኖራትን ወሳኝ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን ደጋፍ እና እምነት ገልጸዋል።
ከዚሁ በተያያዘ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጎልበትን እና በኢትዮጵያ ሰላም እና ብልፅግና እንዲሰፍን ጠቀላይ ሚኒስተር ዐቢይ (ዶ/ር) በማድረግ ላይ ያሉት ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በቀጣናዊ የደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ በሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ሽብርተኝነት እና የተደራጀ ወንጀልን የመሳሰሉ የደኅንነት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፣ ኬንያ በዓለም ዙሪያ መረጋጋት እንዲኖር ከአጋሮች እና ከሌሎች ሀገራት ጋር አበክራ ትሠራለች ብለዋል።
የሀገሪቱ የፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማትም ለኢትዮጵያ አቻዎቻቸው አስፈላጊውን ትብብር እንዲለግሱ መመሪያ መስጠታቸውንም ከበሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።