AMN-ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም
ሁሉንም የሚያስማማ ሀቅ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ሚካኤል አርቴታ ተጫውቶ ያሳለፈበትን ክለብ በአሰልጣኝነት ከተረከበ በኋላ ብርቱ ተፎካካሪ አድርጎታል።

በርካቶች ከኤፍ ኤ ካፕ ውጪ አለማንሳቱን ደጋግመው ያነሳሉ። አንዳንዶች ደግሞ አርሰናል አርቴታ ከመምጣቱ በፊት የነበረበት ሁኔታ መረሳት የለበትም ባይ ናቸው።
አስተያየቱ ሚዛናዊነት ከታከለበት አርሰናል መሻሻሎችን አሳይቷል። ስፔናዊ አሰልጣኝ ወደ ለመደው ቤት አለቃ ሆኖ ሲመጣ አርሰናል የሊግ ዋንጫ ከሸነፈ 15 ዓመት አልፎታል።
በቻምፒየንስ ሊግ መፎካከሩ ቀርቶ ተሳትፎው እንኳን ዳገት ሆኖበት ነበር። አሁን የተፎካካሪነት ከፍታውን ሰቅሎታል።
የዘንድሮውን ከጨመርን ባለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት ውስጥ ቢያንስ በአንዱ የሊግ ዋንጫ ማሸነፍ ነበረበት። ጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውት ይህ አልተሳካም። አርቴታ አሁን የሚቀረው ለትልልቅ ዋንጫዎች መፎካከር ሳይሆን አሸንፎ ማሳየት እንደሆነ ይነገራል።
ዘንድሮ ብቸኛ ተስፋው ቻምፒየንስ ሊግ ነው። ብርቱ ባላጋራ ገጥሞት የመጀመሪያውን ጨዋታ በገዛ ሜዳው ተሸንፏል። ዛሬ ምሽት ውጤቱን ቀልብሶ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ፍፃሜ ለመድረስ መጣር ይኖርበታል።

አርሰናል በቻምፒየንስ ሊጉ በመጨረሻ ካደረጋቸው አራት የሜዳ ውጪ ጨዋታ አሸንፏል። ዛሬ ከደገመ አምስት ጨዋታ በማሸነፍ በክለቡ አዲስ ታሪክ ይፃፋል።
ከምንም በላይ ድል ከእነርሱ ጋር ከሆነ ከ19 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ ይሆናሉ።
በዛሬው ጨዋታ ሪካርዶ ካላፊዮሪ ይመለሳል። በመጀመሪያው ጨዋታ በቅጣት ሳይሰለፍ የቀረው ቶማስ ፓርቴም የቡድን ስብስቡ አካል ነው። ጋናዊው አማካይ ቡድኑ በኤምሬትስ ተወስዶበት የነበረውን የአማካይ ክፍል ብልጫ ለመመለስ አጋዥ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ፓሪሰን ዠርመ 1ለ0 እየመራ እንደመግባቱ ምንም የሚያጣድፈው ነገር የለም። እዚህ የደረሱት በዕድል አይደለም ፤ ድንቅ ብቃት አሳይተው አንዳንዴም ከእነርሱ በላይ ግምት የተሰጣቸውን ተጋጣሚዎች በመርታት ጭምር እንጂ።
በዛሬው ጨዋታም በፒ ኤስ ጂ በኩል የተለየ ነገር አይጠበቅም። የውድድር አመቱ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኡስማን ዴምቤሌ ከጉዳቱ አገግሞ ይገባል። አርሰናልን በፓርከ ደ ፕሪንስ የሚጠብቁት በተሟላ ስብስብ ነው።
ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚጀምረውን ጨዋታ በውዝግብ የተሞላ የዳኝነት ሕይወት ያላቸው ጀርመናዊው ፍሊክስ ዝዌይር ይመሩታል።
እንደትላንት ምሽቱ ኢንተርሚላን እና ባርሰሎና ጨዋታ ስሜትን ሰቅዞ ለአፍታ አይን የማያስነቅል ጨዋታ ባይሆን እንኳን በዛሬውም ፍልሚያ ድንቅ ፉክክር ይጠበቃል።
በሸዋንግዛው ግርማ