አርበኝነት በኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ቀለም የተጻፈ ነው፡፡ በተለይ ከ1928 ዓ.ም በኋላ አርበኝነት ከማንነት፣ ከክብር እና ከነጻነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ “በዘመኑ ፋሺስት ጣሊያን በ1888ዓ.ም በኢትዮጵያ በዓድዋ የደረሰባትን መራር ሽንፈት ለመበቀል 40 ዓመታትን ዝግጅት ካደረገች በኋላ ለመላው የጥቁር ሕዝብ እንደ ነጻነት ምልክት ተደርጋ የምትታየውን ኢትዮጵያን ዳግም ወረረች። የኢትዮጵያ ሕዝብም በአንድነት የጣሊያንን ወረራ ለመከላከል ጨርቄን ማቄን ሳይል ተነሳ” ይላል ሀሁ መጻሕፍት ገጸ-ድር ጉዳዩን አስመልክቶ ባሰፈረው መረጃ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በመድፍ እና በአውሮፕላን መርዝ በታገዘው የጣሊያን ጦር ተሸነፍን ብለው ተስፋ አልቆረጡም። እጅም አልሰጡም፡፡ የሀይማኖት አባቶች “እንኳን ሕዝቡ የኢትዮጵያ ምድር ለባዕድ እንዳይገዛ” በማለት አውግዘው መሰዋዕትነት ከፈሉ፡፡ ቆራጦችም የአርበኝነት ትግል ለማካሄድ ዱር ቤቴ አሉ፡፡ በዚህም እንደ እጃቸው መዳፍ ጠንቅቀው የሚያውቁትን የሀገራቸውን መልክዓ-ምድር መመኪያ አድርገው ፋሽስት ጣሊያንን ይፋለሙ ጀመር፡፡
ከአምስት ዓመት ተጋድሎ በኋላም ጣሊያን ድጋሚ የሽንፈትን ጽዋ ተጎነጨች፡፡ አርበኞች በዱር በገደሉ ባደረጉት ትግል የኢትዮጵያ ነጻነት ዳግም ተረጋገጠ፡፡ ሰንደቅ ዓላማውም ከፍ ብሎ ተውለበለበ፡፡ ይህ የአርበኞች ድል መታሰቢያ በአልም ሚያዝያ 27 ቀን ይከበራል፡፡ ዘንድሮም የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በመጭው ሰኞ ለ84ኛ ጊዜ በድምቀት ይከበራል፡፡ ከነጻነት ተጋድሎ እስከ አሁን ድረስ ግን አርበኞችን በማበረታታት፣ በማወደስ እና ገድላቸው ታሪክ ተሻጋሪ እንዲሆን ኪነ-ጥበብ ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም እለቱን ታሳቢ በማድረግ ስለ አርበኞች የተሰሩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች እና የሀገር ፍቅር ስሜትን ከፍ ለማድረግ ያላቸው ሚና ላይ አጭር ዳሰሳ አድርጓል።
በሀገራችን አርበኝነት የሚያወሱ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች፣ የህዝብ ግጥሞችና ስዕሎች ተሰርተዋል፡፡ በፊልሙ ዘርፍ ቀዳሚው ተጠቃሽ “የአርበኛው ልጅ” ፊልም ነው፡፡
ይህ ፊልም ለእይታ የበቃው ከ10 ዓመት በፊት ነው፡፡ ካሳሁን ፍስሃ(ማንዴላ)፣ የትምወርቅ ኑርበዣ፣ ሰለሞን ተካ፣ ጌታቸው ታሰደ እና ሌሎችም በትወና ተሳትፈውበታል፡፡ የአውሮፓ ሀገራት ግዛታቸውን ሊያስፋፉ የቅኝ ግዛት አስተሳሰባቸውን ይዘው ተንቀሳቀሱ። አህጉረ አፍሪካም ምርጫቸው ነበረች። ኢትዮጵያም ከችግሩ ገፈት ቀማሽ ነበረች። በመጨረሻም በቆራጥ አርበኛ ልጆቿ የነጻነት ሰንደቋን ማውለብለቧን በፊልሙ ተንጸባርቋል፡፡ በፊልሙ ላይ አንድ አርበኛ የነበሩ አባት ልጅ ሲወለድላቸው የሚሰማቸው ደስታ እና ሀገሩን እንዲጠቅምና ኢትዮጵያን እንዲያስጠራ ያላቸውን ፍላጎት ሲገልጹ ይታያል፡፡
“ጀግና ይሞታል ብሎ ማን ነው የተናገረው
ዘሩን ሳይተካ ክብሩን ሳያወርሰው
በስተርጅና መጣ አባት መተኪያ
ተወልዷል ጀግናዬ ለእምዬ ኢትዮጵያ…” በማለትም ስሜታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የአርበኛው ልጅም አድጎ ፖሊስ ሆነ፡፡ ይሁንና በሙያው ስኬታማ አልነበረም። የኋላ ኋላ ህልማቸው ተሳካ። ልጃቸው በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ፊት፣ በመዝሙር ታጅቦ ማህበረበሱን ለማገልገል ቃል ገባ፡፡ በአንድ በትምህርት ቤት ሲያልፉም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል በክብር የሚቆም በታዳሚዎች ዘንድም እንደአርዓያ የሆነ ልጅ ሆነላቸው።
አንድ ቀን ልጃቸው ከአዳጊህጻናት መካከል በመለዮው በክብር ቆሞ ሰንደቅ ዓላማ ሲያከብር አባት በዚያው መንገድ ሲያልፉ ተገናኙ፡፡ ልዩ ስሜትም ተሰማቸው፡፡ እንዲህም አሉት፡፡
“ልጄ ዛሬ አለሜን ነው ያሳየኸኝ። ሞቴ በዚህ ሰዓት ቢሆን በደስታ አንቀላፋለሁ፡፡ ጀግንነት በየፈርጁ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብዙነት ነው፡፡ ቋንቋችን ቢለያይም ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ ይህን ማጽናት ደግሞ የአንተና የሌሎች የህግ ሰዎች ሃላፊነት ነው፡፡ ፍቅርና ሰላም ካለ እድገትና ብልጽግና ወደ ሀገራችን ይመለሳል፡፡ ይህ ካልሆነ ፈጣሪ ፊቱን ያዞርብናል“ በማለት ልጃቸውን በግብረገብነትና በምክር ለሀገሩ የሚጠቅም ሰው እንዲሆን ሲደክሙ ያሳያል፡፡ መጨረሻም ለህግ ዘብ የሚቆም፣ ወንጀለኞችን ለህግ የሚያቀርብና ሀገር ወዳድ አዲስ ትውልድ አርበኛ ልጅ አበረከቱ፡፡
“እህት ወንድም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል
እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል
ወዳጅ የሞተ እንደሁ በሀገር ይለቀሳል
ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል” በሚለው መዝሙር ለሀገር መከታ የሆነ ልጅ ሲያበረክቱ ያሳያል፡፡ ይህ ፊልም አርበኝነት ክብር መሆኑን፣ ሀገር መውደድ መሆኑን፣ በየዘመኑም የየራሱ መልካም መገለጫ መሆኑን ከሚያሳዩ የሀገራችን የኪነጥበብ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡
አርበኞች ለኢትዮጵያ ለከፈሉት ነጻነት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከፊልም፣ ከስዕልና ሙዚቃ በተጨማሪም ህዝባዊ ግጥሞችና ቅኔዎች ተሰርተዋል፡፡ አለብነትም፡-
“ምናባቱ ፋሽስት፣
ፋሽስት ምናባቱ፣
እንወጋዋለን በገዛ ብረቱ…” የሚለውን የህዝብ ግጥም መጥቀስ ይቻላል። እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በበኩሏ ዘራፌዋ በሚለው ስራዋ አርበኝነት ሀገርን መጠበቅ፣ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆንና ከራስ በፊት ኢትዮጵያን ማስቀደም እንደሆነ ታወሳለች፡፡
ጀግና ደስ ይለኛል ሲታጠቅ ማለዳ
ጎበዝ ደስ ይለኛል ሲታጠቅ ማለዳ
የሚያበላ መስሎ የሚሸኝ እንግዳ
አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት
እያደር ይፈጃል እንደ እግር እሳት … በማለት፡፡
በእርግጥም ሙዚቃ ብሔራዊ ማንነትን በማጎልበት፣ አርበኝነትን በማውሳት፣ አንድነትን በመፍጠር እና የጋራ ባለቤትነት ስሜትን በማጎልበት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ “The Role of Music in Warfare, Patriotism, and Nationalism” እ.ኤ.አ በኮል ማንድራስ የተጻፈው ጽሑፍ እንደሚያትተው ሙዚቃ የሀገር ፍቅርን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ የአርበኞችን ታሪክ ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁነኛ መሳሪያ ነው፡፡ ለአርበኞች የሚሰሩ ዘፈኖችም ብሔራዊ ስሜትን የሚያንፀባርቁ እና ለሀገር ዳር ድንበር መዋደቅን የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
ሀገራዊ ሙዚቃ ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የታሪክ ክስተቶችን እና የአባቶችን ገድልና ታሪኮችን በማቅረብ ወጣቱ ትውልድ በየዘርፉ የዘመኑ አርበኛ እንዲሆን መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ ሙዚቃ አርበኝነትን ከመዘከር አንጻር ያለው ፋይዳ በብዙ አይነት መልኩ ሊታይ ይችላል ይላል ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ፡፡ ሙዚቃ የአርበኞች ታሪክን እና ትውልድ ማስተሳሰሪያ ዋነኛ ገመድ ነው፡፡ ትናንትን የሚዘክር ነው፡፡ ዛሬን የሚሰራ ነው፡፡ በትናንትናና በዛሬ ትውልዶች መካከል የስሜትና የሀገር ፍቅር ትስስር የሚሰራበት መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በሙዚቃ፣ በሽለላ፣ በቀረርቶ ታግዘው ውድ ህይወታቸውን ከፍለው ፋሽስትን ድል ነሱ፡፡ ለዚህም ነው ኪነ ጥበብ ትናንት በነጻነት ትግሉ ወቅት አርበኞችን በማበረታታት ዛሬ ላይ ደግሞ ታሪክን በመዘከር ሁነኛ መሳሪያ ነው የምንለው፡፡
“እናንተም ወዲህ ኑ እኛም
እንመጣለን
አረበረከቴ ላይ እንገናኛለን፡፡
ገዳይ እቁኒ ላይ ሾላ መገናኛ፡፡
ምናባቱ ፋሽስት፣ ምናባቱ
በረዢም ቁመቱ፣
በደንዳና ባቱ፣
እንወጋዋለን በገዛ ብረቱ…” እያለ የሀገራቸውን ዳር ድንበርና ነጻት ሳያስነኩ ዛሬ ደርሰዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ሰርጸ ፍሬስብሓት በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ በተዘጋጀ “የኢትዮጵያ አርበኝነት” የተሰኘ የኪነ ጥበብ አውደ ርዕይ ላይ ባደረገው ንግግር አርበኝነትና ኪነ ጥበብ ትልቅ ትስስር አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ነገረ-ጭብጥ ላይ ምን ያህል ተሰርቷል የሚለው መታየት አለበት ይላል፡፡
በተለይ ሙዚቃና ግጥም የተለመደ ነው የሚለው ባለሙያው ስዕል አርበኝነትን ከመተረክ እና በማውሳት አንጻር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም በበርካቶች ዘንድ አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመኑ የገጠማትን ፈተናዎች አባቶቻችን እንዴት እንደተሻገሩት በማሳየት ረገድ ኪነ ጥበብ በተለይ ደግሞ ስዕል ጥሩ መስታወት ነው ሲልም ተናግሯል፡፡
ከግጥም፣ ከሙዚቃ እና ከፊልም በተጨማሪ ስዕልም የሀገር ፍቅር እና የአርበኞችን ተጋድሎ በመዘከር ተጠቃሹ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ሥዕል ብሔራዊ ማንነትን፣ ታሪክንና ባህላዊ እሴቶችን በምስል በመወከል የሀገር ፍቅርን በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። ጀግኖችን ማሳየት፣ ስኬቶችን ማጉላት እና የሀገሪቱን ፈተናዎች እና ድሎች በማስመዝገብ አወንታዊ ሀገራዊ ትረካዎችን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ ይጠቅማል። ይሁን እንጂ በሀገራችን የአርበኞችን ትግልና ታሪክ የሚያወሱ በርካታ የስዕል ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በጊዜው አማረ