የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እና አትሌቶች የኢትዮጵያ ብራንድ ሆነው ለዓመታት ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቀደምት ከሆኑት የስፖርት አደረጃጀቶች መካከልም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ውድድሮች ያስመዘገበቻቸው አንፀባራቂ ውጤቶች ከአትሌቲክሱ ጋር የተያያዙ ለመሆናቸውም በርካታ የትራክና የፊልድ የድል ታሪኮችን በእማኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ስፖርት በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚል መጠሪያ ከተመሠረተ ከ70 ዓመታት በላይ ሆኖታል። ፌዴሬሽኑ የሚመራው በየአራት ዓመቱ በሚመረጡ ፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ነው፡፡ በታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም በተከናወነው 28ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውም ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩ አመራሮች ተሰይመዋል፡፡ እነዚህ አመራሮች አትሌቲክሱን ወደቀደመ ክብሩ የመመለስ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
በተለይም ከወራት በፊት በተከናወነው የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በምትጠበቅባቸው ርቀቶች ውጤት አለማምጣቷ፣ በውድደሩ ውስጥ ውዝግቦች መስተዋላቸውና መሰል ጉዳዮች ደግሞ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ቀጣይ የቤት ስራ የበዛ ስለመሆኑ አመላክቷል፡፡
አዲሶቹ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች ወደ ስራ ከገቡ በኋላ ከሰሯቸው ስራዎች መካከል ከአትሌቲክስ አሰልጣኞችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ማካሄድ ነበር፡፡ በውይይቱም የአትሌቲክስ አሰልጣኞች ደረጃ አሰጣጥ ክፍተቶች፣ የመወዳደሪያ እና የብሔራዊ ቡድን አትሌቶችና አሰልጣኞች ምርጫ እንዴት መመራት አለበት? የሚሉ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ስልጠና፣ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ኢንስትራክተር ሳሙኤል ብርሃኑ የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት አትሌቶች በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ስልጠና ውድድሮች ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ፣ ተተኪዎች በጥራትና በብዛት ማፍራት የሚችሉ አሰልጣኞች በየደረጃቸው በመለየት ወጥነት ያለው አሰራር ማስፈን ወሳኝ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ይገልጻሉ፡፡
የአትሌቲክስ ክለቦች ሲፈርሱ ዝም ብሎ መመልከት፣ ድጋፍ እና ክትትል አለማድረግ፣ የሴት አሰልጣኞችን መብት በበቂ ሁኔታ አለማክበር እና ልምድና ውጤት ያላቸውን አሰልጣኞች ትኩረት አለመስጠት የተስተዋሉ ችግሮች ስለመሆናው ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በመረጃው መሠረት፣ የልምምድ መስሪያ ቦታዎች ችግር መኖርና አትሌቶች ለውድድር የሚመረጡበት መስፈርት ላይ ግልፀኝነት ማነስ በአትሌቲክሱ ዙሪያ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህ ችግሮች ታዲያ መንስኤያቸው የተለያየ ቢሆንም በዋናነት የአትሌቶችና የአሰልጣኞች ደረጃ መመሪያ በተሟላ መልኩ ባለመተግበሩ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ይገልጻል፡፡ መመሪያውም በየ2 ዓመቱ እደሚታደስ እና ከዓለም ሻምፒዮና ውድድር በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
ለመሆኑ ይህ መመሪያ በውስጡ ምን ይዟል? ተግባራዊ ሲደረግስ የትኞችን ችግሮች ይፈታል? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን መፈተሽ ደግሞ ተግቢነት ይኖረዋል፡፡ ከወራት በኋላ ከሚደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው መመሪያ ውድድር በመጣ ቁጥር ሲያጨቃጭቅ ለነበረው የአሰልጣኞች እና የአትሌቶች የምርጫ ጉዳይን ለመፍታት ሁነኛ አማራጭ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን ያብራራሉ፡፡
ለአስር ዓመት ያልተደፈረውና የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት መስፈርትና የአሠልጣኞች ደረጃ የጥናት መመሪያን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና አትሌቶች የሚመረጡበት ግልጽ የሆነ መስፈርት ያስቀምጣል ተብሏል። እንደዚሁም አሠልጣኞች ተመዝግበው በፌዴሬሽኑ ሲስተም (ዳታ) ውስጥ መግባት እንዳለባቸው አስገዳጅ ህግ የሚቀመጥ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በአጭርና ረዥም ጊዜ የሚሰጡ ስልጠናዎችንም መስመር ለማስያዝ ያግዛል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ሻምበል ቶለሳ ቆቱ በበኩላቸው፣ አሰልጣኞች የአትሌቲክስ ስፖርት ቁልፍ ናቸው ይላሉ፡፡ እንደዚህ አይነት መመሪያዎችን ወደ ተግባር ማስገባት ከተቻለ ለአትሌቲክሱ እድገት ወሳኝ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ በተለይም የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ጨምሮ በተለያዩ የውድድር መድረኮች ላይ የሚሳተፉ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶችና አሰልጣኞችን ግልፅ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነት ባለው ስርዓት በመምረጥ ውጤታማ የሆኑ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች እና አሰልጣኞችን ማፍራት ያስችላልም ብለዋል ሻምበል ቶለሳ ቆቱ፡፡
የአትሌቲክስ ስፖርት ጋዜጠኛ ወርቅነህ ጋሻው በሰጡን አስተያየት፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የዘርፉን ችግሮች ከስር መሰረቱ መፍታት ከፈለገ አትሌቲክሱ የገባበት ችግር ውስብስብ መሆኑን ማመን ይኖርበታል፡፡ ቀጥሎም በአትሌቲክሱ የሚስተዋሉ እንደ ተቀናጅቶ አለመስራት፣ ያልዘመኑ የስልጠና እና የታክቲክ ችግሮች፣ የአሰልጣኞችና አትሌቶች ምልመላ ሂደት ላይ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ተገንዝቦ እነዚህን ለማስተካከል መስራት ይኖርበታል የሚል ምክረ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
በጋዜጠኛው አስተያየት የሚስማሙት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር አሰግድ ከተማም የሚዘጋጁ መመሪያዎችን ወደ ተግባር መቀየር፣ ወቅቱን የሚመጥን የስልጠና ማንዋል ማዘጋጀት፣ ፌዴሬሽኑ ከየት ተነስቶ ወዴት መሄድ እንደሚፈለግ ማዘጋጀት እንደሚገባም ያብራራሉ፡፡
ለአትሌቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ለባለሙያዎች ነፃነት መስጠት እንደሚገባም በተጨማሪነት ይጠቅሳሉ። አመራሩ አሁን በጀመረው መልኩ ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ለእነዚህ ችግሮች ቅድሚያ ሰጥቶ ከሰራ መፍትሄ ይኖራል ሲሉም የአትሌቲክስ ስፖርት ጋዜጠኛው ወርቅነህ ያስረዳሉ፡፡ እንደዚሁም አትሌቲክሱን በማዘመን ለአዳጊዎችም ጭምር የተስተካከለ የአሰራር ስርዓት በመፍጠር ያለንን መልካም ገፅታ ማስቀጠል ይገባናል፡፡ የአዲሱ አመራር ቀዳሚ ስራም ይህ ሊሆን እንደሚገባ መምህር አሰግድ አክለው ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ ወርቅነህና መምህር አሰግድ በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ የአትሌቲክሱ አመራር ከቢሮክራሲ ስራ ተላቅቆ ከታች ጀምሮ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በሚለው ሀሳብ ላይ ይስማማሉ፡፡
በተለይም አሰልጣኞች የሚመለመሉበትና አቅማቸው የሚገነባበትን አሰራር በወጥነት መዘርጋት ከተቻለ ምናልባትም ኢትዮጵያን በአትሌቲክሱ ዘርፍ ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ማሳደግ እንደሚቻልም አስተያየት ሰጪዎቹ ያስረዳሉ፡፡ “ብቁ አሰልጣኝ ካለ ብቁ አትሌትን ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ” የሚሉት ጋዜጠኛ ወርቅነህ ደግሞ የስፖርት ልማት ስራ ላይ ማተኮርና የአትሌት አሰልጣኞች ላይ መስራትም ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ስለመሆኑ ያብራራሉ፡፡
ከልማዳዊ አሰራር በመውጣት ዘመናዊውን አሰራር መከተል ከአዲሱ የአትሌቲክስ አመራር የሚጠበቅ ነውም ብለዋል፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ወርቅነህ አስተያየት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በመላ ሀገሪቱ የአትሌቲክስ ስፖርትን በማስፋፋት ተተኪ አትሌቶችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ቁልፍ አካላት አሰልጣኞች ናቸው፡፡ በመሆኑም እነሱ ላይ አተኩሮ መስራት ይገባል፡፡
የፓሪስ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቱ አትሌት ታምራት ቶላ የቡዳፔስቱን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአስረጅነት አንስቶ የሰጠውን አስተያየት ደግሞ እዚህ ጋር እንጥቀስ። አትሌቱ በወቅቱ በሰጠው አስተያየት ለተበላሸው ውጤት ኃላፊነቱን መውሰድ ያለባቸው አትሌቶች እንዳልሆኑ ገልጿል። ለጠፋው ውጤት በዋናነት ኃላፊነት የሚወስደው ፌዴሬሽኑ እና አሰልጣኞች ናቸው ማለቱም የሚታወስ ነው፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንደ ኦሎምፒክ ባሉ የውድድር መድረኮች ላይ ትታወቅበት ወደ ነበረው ደረጃ በአንድነት መንፈስ ለድል የመፋለም ወኔ እንዲመለስ የአሰልጣኞች ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። በተለይም የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ለዚህ ከፍተኛውን ድርሻ እንሚወስዱም ያታወቃል፡፡ በመሆኑም የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት ከተደበላለቀ አሠራር ወጥቶ መስፈርት ተዘጋጅቶለት፣ የአሠልጣኞች ደረጃም በግልጽ ተለይቶ በወጣለት መመሪያ መሰረት መስራት ይገባል የሚለውም የባለሙያዎች አስተያየት ነው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ