
AMN- ጥር 12/2017 ዓ.ም
በምክትል ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአዳማ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ በአንድ ማዕከል ለመስጠት የተቋቋመውና “ጋዲሳ ኦዳ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ጎብኝተዋል።
ጉብኝታቸውን አስመልክተው አቶ አደም በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ 29 ሴክተሮችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አግባብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ስርዓት የባለጉዳዮችን እንግልት የቀነሰ፣ ገቢን ለመሰብሰብ ምቹ የሆነ፣ ልማዳዊ የሆነውን የወረቀት ስርዓት ከ80 ፐርሰንት በላይ በሁሉም ሴክተሮች ውስጥ ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም የአሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ከፍተኛ እድል የፈጠረ መሆኑን አይተናል ነው ያሉት።
የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ደረጃ ያሉ ተቋማትን በአንድ ማዕከል ከማሰባሰብ ባሻገር የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ተቋማትም በአንድ ማዕከል እንዲሰሩ ማድረጉ እጅግ የሚበረታታ እና ለሌሎች ከተማ አስተዳደሮችም ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች መሬትን ሙሉ ለሙሉ በካድስተር ቴክኖሎጂ ዲጅታል ለማድረግ የተሄደበት ርቀት፣ በከተማዋ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የተዘረጋው የሲሲቲቪ ካሜራ ዝርጋታ ውጤታማነት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በምርጥ ተሞክሮነት ተወስዶ ተግባራዊ እንዲደረግ እንደ ብልፅግና ፓርቲ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በቀጣይ የሚሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።