
AMN ህዳር 21/2017 ዓ .ም
በሐረሪ ክልል እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለ ስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ መሃመድ አብዱረህማን (ኢ/ር) የተመራ ልዑክ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ተመልክቷል፡፡
ልዑካን ቡድኑ የመስክ ምልከታውን ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተገኙበት ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
አቶ ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት÷ የኮሪደር ልማቱ በክልሉ እና አካባቢው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተሳሰር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
በተለይ በኮሪደር ልማት ዘርፍ በፌዴራል ደረጃ ለክልሉ የሚደረገው ድጋፍ ከተማዋን የተሻለ ገፅታ በማላበስ ለኑሮ እና ስራ ምቹ የሆነች ከተማን ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል።
መሃመድ አብዱረህማን (ኢ/ር) በበኩላቸው ÷በክልሉ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው አበረታች ውጤቶች እንደተመዘገቡ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡