
AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ የዋጋ ንረትን በማረጋጋትና ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት በመገንባት ጥራት ያለው የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
የባንክ ሥራ አዋጅ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ እንደሆነም ተገልጿል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ11ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ እና የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል።
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ፣ አዋጆችን በተመለከተ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ፥ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ስርዓትን መፍጠር ያስችላሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በባንኩ የማሻሻያ አዋጅ ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ባንኩ አሰራሩን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር በማናበብ ማዘመን እንዳለበት ጠቁመዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በውጤታማነት ለመምራትና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መርሆ ጋር የተጣጣመ ማዕከላዊ ባንክ ለመሆን አዲሱ አዋጅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ባንክ አዋጁ የባንኩን ቁልፍ ተልዕኮዎች በግልፅና በቅደም ተከተል ማስቀመጡ ከዚህ ቀደም የነበሩ በአሰራርና በፋይናንስ ስርዓቱ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን እንደሚቀርፍ አብራርተዋል።
የዋጋ ንረትን በማረጋጋትና ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት በመገንባት የምጣኔ ሃብት ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ባንኩ ጉልህ ሚና እንዲጫወት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አዲስ በጸደቀው የባንክ ሥራ አዋጅ ላይ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤቱ አባላት፥ የሀገር ውስጥ ባንኮችን አቅም ሳያሳድጉ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረግ ይዞት ሊመጣ የሚችል አሉታዊ ተፅዕኖ የለም ወይ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በሰጡት ምላሽ፣ አዋጁ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና ለምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ቀጣይነት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ስራ መሰማራታቸው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ከማምጣት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ ያግዛልም ነው ያሉት።
የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት ማድረግ የሀገር ውስጥ ባንኮችን አቅም የሚያጠናክር እንጂ የሚያጠፋ አለመሆኑንም አብራርተዋል።
አሰራሩ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ተቀጥላ ኩባንያ እንዲከፍቱና ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ባንኮች እያደገ ለመጣው የኢኮኖሚ ዕድገት ምላሽ የሚሰጥ አቅም ማጎልበት ይገባቸዋል ያሉት ገዥው፣ ለዚህ ደግሞ ውህደት በመፍጠር ሃብታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።