አዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ህብረተሰቡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው- ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር)

You are currently viewing አዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ህብረተሰቡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው- ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር)

AMN – የካቲት 15/2017 ዓ.ም

አዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሌብነት እና ብልሹ አሰራር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊው ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ እንደ ሀገር ሀገረ መንግስት ግንባታው ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅሩ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ እንዲሆን ለማድረግ አዲሱ አዋጅ ማስፈለጉን አብራርተዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ አዲስ የወጣው አዋጅ፣ ለህብረተሰብ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል፣ ሥርዓት በተለወጠ ቁጥር የማይለወጥ፣ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የሲቪል ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያስችልም አክለዋል።

በተጨማሪም ከአደረጃጀት፣ ከአመራር እና አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማሻሻል ጠቀሜታ እንዳለውም አስገንዝበዋል።

የበፊቱ አዋጅ ከአዲሱ የሚለይበትም፣ የበፊቱ በመንግስት ሰራተኛው መብት እና ግዴታ ላይ ያተኮረ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለማረም በሚያስችል መልኩ የተቀረፀ ስላልነበረ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review