አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ምላሽ እንዲያገኙ ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የምክር ቤት አባላቱ ኤ ኤም ኤን የሚያከናውናቸውን የቴክኖሎጂና የአሰራር ሂደቶችን ጎብኝተዋል።
ለጎብኝዎች ገለፃ ያደረጉት የቴሌቪዥን የዜናና ወቅራዊ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ገመቺስ ምህረቴ፣ ሚዲያው ተደራሽነቱን ለማስፋት በተለያዩ አማራጮች እና በብዝሃ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ሚዲያው የትውልድ ድምጽ በመሆን ትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረጉን አቶ ገመቺስ አመላክተዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ በበኩላቸው፣ ተቋሙ ባከናወነው ሪፎርም መሰረት አሁን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የለውጥ ሂደቱ አመላካች ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቆሙ በአገልጋዩ፣ በዋርካ ፕሮግራሞችና በዜና ዘገባው የጀመራቸውን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምላሽ እንዲያገኙ የሚሰራቸው ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በተያያዘም ከተለያዩ የመንግስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች የኤ ኤም ኤንን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
ሚዲያው፣ በኤ ኤም ኤን ፕላስ እየሰጠው የሚገኘው ትምህርት በቴሌቪዥን ለትምህርታችን አጋዥ ሆኗል ብለዋል ተማሪዎቹ፡፡
የጉብኝቱ ተሳታፊ መምህራን እና ተማሪዎች በኤ ኤም ኤን የሚሰጠው የቴሌቪዥን ትምህርት፣ ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባሻገር በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሂደት ምቹ አድርጎታል ብለዋል።
ተማሪዎቹ ነገ ሀገር የሚረከቡና የሚገነቡ በመሆናቸው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን ማየትና መተዋወቅ እንዲሁም መተግበር ተገቢነት እንዳለው በጉብኝቱ ወቅት ተመላክቷል፡፡
በሩዝሊን መሀመድ