AMN-ታኅሳስ 27/2017 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ተቋም በመገኘት ድጋፍ ለሚደረግላቸው ወገኖችን የቁርስ ግብዣ እና የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ስራ አስፈፃሚ መዓረግ የኤኤምኤን የሃብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ዳዲ ተቋሙ ከሚሰራቸው የይዘት ስራዎች ጎን ለጎን ማህበራዊ ሃላፊነቱን የመወጣት ግዴታውን በትኩረት በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የመቄዶኒያ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው ኤኤምኤን በዛሬው ዕለት ላደረገው ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት እና ሰብዓዊ ተግባር እንዲሁም እንደሚዲያ ተቋም የድርጅቱን ማስታወቂያዎች በነፃ ለዓየር በማብቃት እያደረገ ላለው ድጋፍ በአረጋውያኑ እና በድርጅታቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።
መሰል ተግባርን ሌሎች ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በመፈፀም ተቋማቸው በማከናወን ላይ ያለውን ሰው ተኮር የሆነ ሰብዓዊ ተግባር እንዲያግዙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
መቄዶንያ በአሁን ግዜ በ44 ማእከላት ከ ስምንት ሺ የሚልቁ ወገኖችን በመደገፍ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቀን ወጪው ከሁለት ሚሊዮን ብር የተሻገረው ድርጅቱ አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋት እና ተደራሽ ለመሆን የካቲቲ 1 2017 ሰፊ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
መቄዶንያን በመጎብኘት የድርጅቱን እጥረት በመሙላት ሁሉም ጥረቱን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

አቶ ቢኒያም በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለድርጅቱ በሚያደርገው ተከታታይ ድጋፍ አመስግነዋል።
በሹመት ደመቀ