አዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን አዳዲስ እድሎችን የሚከፍት ማዕከል ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን አዳዲስ እድሎችን የሚከፍት ማዕከል ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-የካቲት 22/2017 ዓ.ም

አዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቋል።

ምረቃውን አስመልክተው የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፣ አዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን አዳዲስ እድሎችን የሚከፍት፣ የማያቋርጥ የሃብት ምንጭ መፍጠሪያ የሚሆን እንዲሁም ለገጽታ ግንባታ እና ለቱርስት ስበት ትልቅ ሚና የሚጫወት ማዕከል ነው ብለዋል::

ማዕከሉ አለምአቀፋዊ ኮንፍራንሶችን፣ የንግድ ውይይቶችንና ስምምነቶችን፣ ባህላዊ መድረኮችንና ልዩ ልዩ ኤግዚቢሽኖችን ለማስተናገድ እንዲሁም አዳዲስ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት የንግድና የኢኮኖሚ ስምምነቶች የሚጎለብቱበት መሆኑንም ገልጸዋል::

15ሺ ካሬ የውጪ ሁነት ማስተናገጃ ቦታ ያለው የአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል ባለ 5 ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል፣ ሪስቶራንቶች፣ የስፖርት፣ የጤና፣ የመዝናኛ እና የልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫን ያከተተ ግዙፍ ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህም ባሻገር፣ በአንድ ጊዜ እስከ 2000 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል ፓርኪንግ ያለዉ መሆኑንም አውስተዋል።

የለሚ ፓርክ እና በቀጥታ ከአየር መንገድ ጋር የሚያገናኝ ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማትም ከማዕከሉ ጋር ተያይዞ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ያሉት ከንቲባዋ ፤ይህም ኢኮኖሚያችንን የሚያነቃቃ፣ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑ በላይ እንግዶች ሲመጡ ያለምንም እንግልት ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ እንዲያገኝ ተደርጎ የተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ይህ ስራ ከዳር እንዲደርስ የቅርብ ድጋፍና ክትትል ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review