
AMN – ኅዳር 05/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ሥራዎች በሩብ ዓመቱ መሠራታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ሥራዎች ወጪ ቆጣቢ፣ ጥራት ያላቸው እና ባጠረ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።
ሩብ ዓመቱ ከሕዝብ ጋር ተቀራርበን የሠራንበት፣ የአመራር ቅንጅት የታየበት እና የሥራ ባህልን መለወጥ የተቻለበት ነውም ብለዋል።
የኮሪደር ልማት እና ከተማዋን መልሶ የማደስ ሥራዎቻች ውጤታማ ሆነዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በኮሪደር ልማቱ ለኑሮ ከማይመች ጎስቋላ አካባቢ ያነሣናቸው ነዋሪዎቻችንን ለኑሮ ምቹ የሆነ ንፁህ የመኖሪያ ቤት እና አካባቢ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም የተሻለ እንደነበርም አንሥተው፣ ሁሉንም ሥራ በማስተሳሰር የመምራት እና ለውጤት ማብቃት መቻል አንዱ ጥንካሬ ነው ብለዋል።
ሌብነት እና ብልሹ አሠራር ያልተሻገርናቸው ቢሆኑም ነዋሪው የሚሰጠውን ጥቆማ እና አስተያየትን መሠረት በማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ፍሬ ማፍራት የጀመሩበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ፣ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ለማድረግ እና የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት እመርታ የታየበት ሥራ ተሠርቷልም ነው ያሉት።
አዲስ አበባ በሩብ ዓመቱ ብቻ 20 የተለያዩ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን በብቃት ማስተናገድ መቻሏን፣ በዚህም ብዙ ጥቅሞች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የተቋማት ተቀናጅቶ መሥራት ለውጥ የታየበት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ በዚህ ዘርፍ አንዱ የሠራውን ሌላው የሚያፈርስበት ሁኔታ ቀርቶ በመናበብ የተሠራበት እንደሆነ አብራርተዋል።

የበጎ ፈቃድ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን እና በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን፣ ለአብነትም ከ2 ሺህ 780 በላይ ቤቶች የተሠሩት በበጎ ፋድ መሆኑን እና ሕዝብ እና ባለሃብቱን በማስተባበር ከ5 ቢሊዮን በላይ ብር ለዚሁ ሥራ መዋሉን ገልጸዋል።
ቤቶችን በማስተዳደር፣ በማስተላፍ እንዲሁም በመንገድ ግንባታ ጥሩ ሥራ መሠራቱን አውስተው፣ በተለይም በሩብ ዓመቱ ከ27 ኪሎ ሜትር በላይ በራስ ኃይል የተሠራ ሲሆን፣ ከ221 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች ጥገና ተካሂዷል ብለዋል።
የስማርት ከተማ ግንባታ ሥራዎች ስኬት የተገኘባቸው መሆናቸውን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ በመሬት አስተዳደር እና ልማት ቢሮ በኅብረት ሥራ ኮሚሽን በሲቪል ምዝገባ እና የዜግነት አገልግሎት መስኮች የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ፍሬ ማፍራት የጀመሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራር የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነትን ፈጥሮ ሥራዎችን የመራበት፣ የአመራር ዕድገት እና መረጋጋት የታየበትም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከሩብ ዓመቱ ውጤታማ ሥራዎች በመነሣትም ችግሮችን በዘላቂነት ለማረም የሚያስችል የአመራር ቁመና ለመፍጠር፣ ግልፅነትን ለመጨመር እና ነዋሪውን በማሳተፍ መሥራት የሚያስችል አቅጣጫም አስቀምጠዋል።
በተቋም ግንባታ፣ የሰው ተኮር ሥራዎችን ማጠናከር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ ገቢ አሰባሰብን ማሻሻል፣ የንግድ ሥርዓቱን ማጠናከር፣ ለነዋሪዎቿ የተመቸች ከተማ መገንባት እንዲሁም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ ወደ አገልግሎት ማስገባት እና የ2ኛ ዙር ኮሪደር ሥራን በጥራት እና በፍጥነት ማጠናቀቅ በቀጣይ በልዩ በትኩረት የሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አስገንዝበዋል።
አገልግሎት አሰጣጣችንን ይበልጥ ቀልጣፋ እና ከሌብነት እና ብልሹ አሠራር የፀዳ በማድረግ በትጋት እና በታማኝነት በማሳተፍ መሥራታችንን አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
በዮናስ በድሉ
All reactions:
1010