AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባን ውበት ያላበሷት የልማት ፕሮጀክቶች ለትውልድ የሚሻገሩ ሃብቶች መሆናቸውን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በለውጡ ዓመታት በአዲስ አበባ የተገነቡና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የመልሶ ግንባታና ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
አባላቱ በእንጦጦ፣ ፒያሳ፣ ካዛንቺስ፣ ገላን ጉራና የአቃቂ ቃሊቲ የተቀናጀ የልማት መንደር፣ ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል እንዲሁም ብርሀን የዐይነ ስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የወንዝ ዳርቻ፣ ኮሪደርና መልሶ ማልማት ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የብልጽግና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎቹ መዲናዋን ውበት ያላበሱና ለትውልድ የሚሻገሩ አሻራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ የተሰሩበት ፍጥነትና ጥራት የመፈጸም አቅም ማደጉን ያሳዩና የብልጽግና ፓርቲን ራዕይ በተግባር የገለጡ መሆናቸውን ጠቅሰው ለስራዎች እውቅና መስጠትም ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
ከእነዚህ የልማት ስራዎችም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጥሩ ተሞክሮ የሚወስድበት መሆኑን ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው አዲስ አበባ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር እዚህ መድረስ የማይታሰብ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአመራሩ ጥበብ ዛሬ ላይ ለትውልድ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች የተተገበሩባት መሆኗን ገልጸው እነዚህ ስራዎች በትክክለኛ የብልጽግና ጉዞ ላይ መሆናችንን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
በሌላ ሀገር ውበት ከመደነቅ ይልቅ የራስን በዚህ መልክ ማስዋብ እንደሚቻል የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሯ ብልጽግና ቃል የገባውን ሳይሸራርፍ እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተከናወኑና እየተሰሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ለሌሎችም ጥሩ ተሞክሮ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በአዲስ አበባ በፍጥነትነና በጥራት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉና የከተማዋን ገፅታ የቀየሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የልማት ስራዎቹ የመዲናዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያነቃቁ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡