አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የመልማት ማሳያ ነች- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም

የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል”የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የፎቶ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ከተማ ሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል።

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ያለፉት አመስት የለውጥ ዓመታት የብልጽግና ጮራ የታየባቸው ጊዜያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በእነዚህ ዓመታት በረጅም ጊዜ እንኳን የሚጠናቀቁ የማይመስሉ ልማቶች በአጭር ጊዜ መጠናቀቃቸውን ያነሱት አቶ ተመስገን፤ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የመልማት ማሳያ ነች ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ አካታችነት እና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ የተመሰረተ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀሳብ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ መገንባቱን ገልጸዋል።

ለሀገር ግንባታ በጋራ መስራት እንደሚቻል ብልጽግና አሳይቷል፣ አሁን ደግሞ አሰባሳቢ የሆነውን ገዢ ትርክት ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የፎቶ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ጉዞ እንዲያሳይ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የፓርቲውን የአምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ ከመፃኢው የኢትዮጵያ ተስፋ ጋር አሰናስሎ የተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል።

ፎቶዎቹ ሺ ቃላትን የሚናገሩ ስለመሆናቸውም አመላክተዋል።

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review