AMN – መስከረም 24/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት አምራ እና ደምቃ ሆረ ፊንፊኔን ለማክበር መዘጋጀቷን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ስድስተኛው የኢሬቻ ፎረም በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል ልዩ መሆኑን ገልጸው፣ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት አምራ እና ደምቃ ሆረ ፊንፊኔን ታከብራለች በለዋል።
አዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት ተላብሳ የቱሪዝም መስዕብ በመሆን የገቢ ምንጭ ሆናለችም ሲሉም አክለዋል።
በጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ መንግሥት ሕዝቡን አንድ በማድረግ አዲስ አበባ ተለውጣ የዓለም የቱሪስት ማዕከል እንድትሆን እና ለሆረ ፊንፊኔ ዝግጁ እንድትሆን ማድረጉን አመልክተዋል። ለዚህ የለውጥ ሥራ የተጉትን ሁሉ አመስግነዋል።
መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ቃሉን አክብሮ እና ቃሉን ወደ ተግባር ለውጦ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን ያወሱት ከንቲባ አዳነች፣ በዚህም የመንግሥት እኛ የሕዝቡ መተማመን ማደጉን ተናግረዋል።
ይሁንና አሁንም ብዙ ሥራ እንደሚቀር የገለጹ ሲሆን ባህል እና እሴታችን የቱሪዝም መስህብ ሆኖ ገቢ እንዲያስገን እና የአገርን ኢኮኖሚ በማሳደጉ ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ግባችን ብልጽግና ነው፤ በመሆኑም ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነትን እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን መትጋት አለብን ሲሉም አመልክተዋል።
የኢሬቻ በዓል ባማረ እና በደመቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ያሳሰቡት ከንቲባ አዳነች በዓሉ በተሳካ መልኩ እንዲከበር ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በሰለሞን በቀለ