አዲስ አበባ እያደገችና እየዘመነች የመጣች ከተማ በመሆኗ ይህንኑ የሚመጥን ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት ይገባል’ – ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው

You are currently viewing አዲስ አበባ እያደገችና እየዘመነች የመጣች ከተማ በመሆኗ ይህንኑ የሚመጥን ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት ይገባል’ – ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው

AMN – መጋቢት 28/2017

አዲስ አበባ እያደገችና እየዘመነች የመጣች ከተማ በመሆኗ ይህንኑ የሚመጥን ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተናገሩ።

“ተቋማዊ ሪፎርም ለተልዕኳዊ ስኬት” በሚል መሪ ቃል በአስራ አንዱ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች እና በማዕከል የስራ ክፍሎች ለሚገኙ ለመካከለኛ አመራሮች የተሰጠው ስልጠናዊ ግምገማ ተጠናቋል።

በሪፎርሙ ውጤት የተገኘባቸው ተግባራት እና በሒደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ በመድረኮቹ ገለፃ ተደርጓል።

በወንጀል መከላከልና ምርመራ፣ በፖሊሳዊ ዲሲፒሊንና ስነ-ምግባር እንዲሁም ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፖሊስ ዶክትሪን ጋር ተያይዞ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ስልጠናም ተሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በስልጠናው ማጠቃለያ በሠጡት የስራ መመሪያ ከተማችን እያደገችና እየዘመነች የመጣች በመሆኑ ይህንኑ የሚመጥን ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት የወቅቱ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገልግሎት አሰጣጣችን እርካታን ለመፍጠር የአገልጋይነትን ስሜት የተላበሰ፣ አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃቱ የዳበረ የፖሊስ ኃይል ማፍራትና የተቋማችንን የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በልዩ ልዩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ከከተማ ግብርና ጋር ተያይዞ የተሰሩ የልማትና የግንባታ ስራዎች የአባላት ኑሮ በማሻሻል ተስፋ ሰጪ ተጠቃሚነትን እየተገኘበት መሆኑን ገልፀው ተግባራቱ ተጠናከረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ከሚከናወኑ ውጤታማ ስራዎች ጎን ለጎን በአንዳንድ አመራርና አባላት የሚስተዋሉ የስነ-ምግባር ጥፋቶችን ለማረምና ለማስተካከል የሚደረጉ ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመልካም አስተዳደር መርሆችን እና የህዝብ እርካታን የሚያረጋግጥ አገልግሎት መስጠት ከህዝብና ከመንግሥት የተሰጠን አደራ ነው ብለዋል።

በተለይም ፖሊስ ከቆመለት ዓላማ ውጪ ተፃራሪ በሆኑ ተግባራት ላይ ተሣትፎ ባላቸው አመራሮችና አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

አገልግሎትን በገንዘብ የሚለውጡ፣ ጎቦ የሚቀበሉ፣ ፍትህን የሚያዛቡና በአጠቃላይ ከፖሊስ ሙያዊ ዲስፒሊን በተቃራኒ መቆም ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አሳስበዋል።

ከሚወሰዱ አስተማሪ እርምጃዎች ጎን ለጎን የአባላትን ስብዕና በመገንባት፣ አጥፊዎችን በመቆጣጠር በኩል በየእርከኑ የሚገኙ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በተጠያቂነት መንፈስ ሊወጡ እንደሚገባ ጥብቅ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በስልጠናው ላይ የተካፈሉ የፖሊስ አመራሮችም ስልጠናው በመደበኛው የፖሊስ ስራቸው ላይ ክፍተቶቻቸውን ያረሙበት እና ጠንካራ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫን ያመላከተ መሆኑን ገልፀው ለቀጣይ ስራቸው ጥሩ ግብአት ያገኙበት ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሁሉም መድረኮች ላይ የተሳተፉ ሰልጣኝ አመራሮች ባለ አስራ አንድ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስልጠናው ተጠናቋል፡፡ በቀጣይ ሥልጠናው እስከ አባሉ ድረስ በተዋረድ እንደሚሰጥ ከከተማዉ ፖሊስ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review