
AMN ግንቦት 12/2017 ዓ.ም
የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ዓለም አቀፍ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ እያስተናገደች ባለችው ዓለም ዓቀፉ የID4 for Africa 11ኛ ጉባኤ ላይ በፋይዳ ምዝገባ እና በወሳኝ ኩነት ቅንጅታዊ ትግበራ ላይ የተገኙ ውጤቶችን እና ልምዷን ለጉባኤው ማካፈሏን ገልጸዋል፡፡

በመዲናችን የሲቪል ምዝገባ ሽፋንን በማስፋት ዘርፉን ለመለወጥ የተወሰደውን የከተማ አስተዳደሩ እርምጃ፣ ከፋይዳ ስርዓት ጋር እየተተገበረ ያለውን ቅንጅት እንዲሁም የተገኘውን ውጤት ለመድረኩ ማካፈላቸውንም ከንቲባ አዳነች ጠቁመዋል፡፡
ከንቲባዋ አያይዘውም ኮንፈረንሱ የተጀመረውን ዲጂታል ብሄራዊ መታወቂያ /ፋይዳን / በተሟላ ሁኔታ እውን ለማድረግ የሚጠቅም ሲሆን አዲስ አበባም በዚህ ረገድ የተያዘዉን ራዕይ በፍጥነት እየተገበረች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የአይዲ ፎር አፍሪካን ጨምሮ የዓለም የስራ ድርጅት (ILO) እና ሌሎች ኮንፍራንሶች መከናወን የከተማችንን የኮንፍራንስ፣ የቱሪዝም እና የኤግዚቢሽን ማዕከልነት ከፍ በማድረግ እንዲሁም የስራ እድልን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ከመሆኑ ባሻገር የአዲስ አበባን ኢኮኖሚ ስለሚያነቃቃ የዚህ አይነት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።