AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም
አዲስ ያስገባናቸው ድሮኖች ከከተማ ፀጥታ ቁጥጥር ባሻገር የቦርደር ሴኪዩሪቲን የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በቀላሉ መቆጣጠር የምንችልበትን ዕድል ይፈጥርልናል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ።
ኮሚሽነር ጀነራሉ በዋናው መስሪያ ቤት የተደራጀውን የድሮን ፓይለት ማሰልጠኛ ማዕከል መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ጀነራሉ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ፖሊስ ውስጥ የተዋወቀው የድሮን ቴክኖሎጂ ማዕከል ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮች የቴክኖሎጂ ስልጠና አግኝተው በፖሊስ ውስጥ የተሻለ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት የተፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል።
አሁን ላይ በተቋሙ ያለው የድሮን አቅም በፖሊስ የወንጀል መከላከል ሰርቪላንስ እና የምርመራ ስራ ከፍተኛ እገዛ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
በፖሊስ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖሊስ በዘመኑ እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎችን ታጥቆ አያውቅም ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሪፎርሙ አሁን ላይ ከአፍሪካ አምስቱ ምርጥ የፖሊስ ተቋማት ውስጥ ለመግባት እያደረገ ያለውን ጥረት በሚያግዝና ለአፍሪካ ወንድሞችም ልምድ እና ተሞክሮ ማስተላለፍ በሚያስችል መልኩ እየተደራጀ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በሪፎርሙ መንግስት ለፖሊስ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የሀገራችን ፖሊስ ዘመናዊ ትጥቆች እንዲኖሩትና ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ የወንጀል መከላከል ስራዎችን ለመስራት በሚያስችል ሁኔታ አቅሙን እያሳደገ ነው ብለዋል፡፡
እንደአዲስ አበባ ያሉ ትላልቅ ከተሞችን ፓትሮል ለማድረግ የእግረኛ ፖሊስ ሠራዊትን ከድሮን ፓትሮል ጋር በማቀናጀት እና በማዋሀድ የወንጀል መከላከል ስራውን በማቀላጠፍ የሚሰራበት እድል ከመፍጠር ባለፈ አድማዎች ሲያጋጥሙ በተደራጀና በጠንካራ ሠራዊት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በቀላሉ ችግሮችን መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ፈጥረናል ነው ያሉት፡፡
እንደ አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ያሉ መድረኮች ሲኖሩ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን ዘግቶ ቪአይፒዎችን ማስተናገድ የሚያስችል የራሱ የሆነ ኮማንድ ኮንትሮል ያለው ዘመናዊ Road block ተሸከርካሪም በዛሬው ዕለት ተመርቆ ስራ እንዲጀምር መደረጉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡