
AMN – ግንቦት 12/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ስራ መግባታቸው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ በድሬዳዋ ከተማ የተገነባውን የፓዮኔር ሲሚንቶ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማስፋፊያ ፕሮጀክት መርቀዋል።
በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ እና በቻይና ባለሃብቶች አጋርነት የተገነባው ፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፍ አልሚ ባለሃብቶች አጋርነት የዕውቀት ሽግግርና የካፒታል ፍሰትን እንዲሁም ምርታማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ስራ መግባታቸው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ሀገር የጀመረችውን የልማት ጉዞ ከማሳለጥ በላይ አዋጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካም በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በዕውቀት ልማትና ሽግግር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ ያስመሰግነዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡