አፍሪካዊነት በከያኒያን

የአፍሪካን የኪነ ጥበብ ዳራ ከአፍሪካዊ ማንነትና ዕሴት ሃሰሳ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ በቅኝ አገዛዝ ምክንያት የተበረዘውን ሳይሆን ቱባውን ትውፊት አጉልቶ ማሳየት ላይ ይበልጥ ያተኩራል፡፡ በዓለም የሃይል ተዋረድ ውስጥ የተገፋውን ዕሴት ወደ ማዕከል የማምጣት ሂደትም ነው ሊባል ይችላል፡፡ ለዚህ ይመስላል አፍሪካዊ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይበልጥ ከፓን አፍሪካኒዝምና ከጥቁሮች የመብት እንቅስቃሴዎች ጋር በጥብቅ የተሳሰሩት፡፡ በዚህ ጽሑፍም በወርሃ- የካቲት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበረውን “የጥቁሮች ታሪክ ወር” (Black History Month) መነሻ በማድረግ አፍሪካዊ ታሪክን፣ ባህልን፣ ዕሴትን እና ማንነትን አጉልተው በሚያሳዩ የሥነ ጥበብ (በተለይ በስዕልና ቅርጻ ቅርጽ) ሥራዎች ላይ አጭር ዳሰሳ አድርገናል፡፡ 

ወርሃ- የካቲት “የጥቁሮች ታሪክ ወር” (Black History Month) በሚል ስያሜ በየዓመቱ በአሜሪካና በሌሎች ሃገራት ውስጥ በተለያዩ ዝግጅቶቸ ይከበራል፡፡ ወሩ የአፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክ ወር በመባልም ይታወቃል፡፡ ይህን የጥቁሮች ታሪክ ወር በአፍሪካውያንና በአፍሪካ አሜሪካውያን የተመዘገቡ ስኬቶችን እንዲሁም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ያላቸውን ማዕከላዊ ሚና የሚዘከርበት ዓመታዊ በአልም ነው። ከዚህ በተጨማሪ ካናዳና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎች የዓለም ሀገራት የጥቁሮችን ታሪክና አበርክቷቸውን በማውሳት በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል፡፡

አፍሪካዊ ማንነት እና ኪነ ጥበብ

አፍሪካውያን እና ትውልደ- አፍሪካውያን ከያኒያን ተወልደው ባደጉባቸው እንዲሁም ተሰድደው በሚኖሩባቸው የተለያዩ ሃገራት ውስጥ አፍሪካዊ ማንነትን አጉልቶ ለማሳየት ብዙ ጥረዋል፡፡ የአፍሪካን ታሪክ፣ ባህል፣ ዕሴት ትውፊት በጥበብ ሥራዎቻቸው አማካይነት ለማሳየት ረዥም መንገድ ተጉዘዋል፡፡ በዚህ ሂደትም ደምቀው የወጡ በርካታ ከያኒያን አሉ፡፡ እነዚህ እንደ ሙዚቃ፣ ሲኒማ፣ ድርሰት፣ ስዕልና ቅርጻ ቅርጽ ባሉ የጥበብ ውጤቶች አፍሪካዊ ማንነትን እና ዕሴትን አጉልተው ማሳየት ችለዋል፡፡ እንዲሁም የአፍሪካ ስምም በአንድም ሆነ በሌላ በበጎ እንዲጠራ አድርገዋል፡፡

ደራሲና የኪነ ጥበብ ሃያሲ ገዛኸኝ ድሪባ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው አስተያየት በተለይ ከፈረንጆቹ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ወዲህ የአፍሪካውያንና የትውልደ- አፍሪካውያን የጥበብ ሥራዎች በይበልጥ አፍሪካዊ ማንነትን አጉልቶ በማውጣት እና ዕሴቶችን በመጠቀም አህጉራዊ ችግሮችን መፍታት ይቻላል የሚል ቅኝት አላቸው፡፡ እንዲሁም ከ1950ዎቹ ጀምሮ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ትግል የሚያደርጉበት፣ ነጻ የወጡትም እውነተኛ አፍሪካዊ ዕሴቶቻቸውን የሚያስሱበት፣ በአሜሪካና አውሮፓ ደግሞ የጥቁሮችን መብት ህጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ ከፍተኛ ትግል የሚያደርጉበት ጊዜ እንደነበር ያወሳው የኪነ ጥበብ ሃያሲው ገዛኸኝ፤ የአህጉሪቱ ከያኒያንም የዚህ ንቅናቄ አካል ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የጥበብ ስራዎቻቸው ይህን ንቅናቄ የሚደግፉ፣ አፍሪካዊ ማንነትን አጉልተው የሚያሳዩና የተገፉ ዕሴቶችን ወደ መድረክ የሚያመጡ ናቸው ብሏል፡፡

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ለፓን አፍሪካኒዝም የኪነት ንቅናቄ እጅግ ትልቅ የሚባል መነቃቃቶች የታየበት ነው፡፡ በተለያዩ ሃገራት አፍሪካዊ እሴቶች እና የፈጠራ ስራዎች ላይ ያተኮሩ ፌስቲቫሎች የተደረጉበት፣ የባህል ልውውጥ የተከናወነበት፣ ከያኒያን ስለአፍሪካዊ ማንነታቸው በተለያዩ መድረኮች ላይ ተገናኝተው የመከሩበት ዘመን ነው፡፡ ለአብነትም በፈረንጆቹ 1966 በሴኔጋል ዳካር የተደረገው የኪነትና ባህል ፌስቲቫል እጅግ የደመቀና ብዙ የልምድ ልውውጥ ከተደረገባቸው አይረሴ መድረኮች መካከል ነው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን ጨምሮ የተለያዩ የጥበብ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡

አፍሪካዊ ማንነትን በጥበብ ሥራዎች

ዋንጌቺ ሙቱ

ዋንጌቺ ሙቱ በቅርጻ ቅርጽ ቀራጺነትና ሰዓሊነት የምትታወቅ የዘር ግንዷ ከኬንያ የሚመዘዝ አሜሪካዊት አርቲስት ነች። በፈረንጆቹ በ2022 “ፈን ታይምስ ማጋዚን” በገጸ- ድሩ እንዳስነበበው፣ ዋንጌቺ ሙቱ በሥነ ጥበብ ስራዎቿ ጾታን፣ አፍሪካዊ ማንነትን፣ የሥነ ጥበብ ታሪክን እና የግለሰብ ማንነትን በማጣመር በጥበብ ሥራዎቿ አጉልታ በማሳየት ትታወቃለች። ሁለገብ የሥነ ጥበብ አርቲስት የሆነችው ዋንጌቺ ሙቱ ቅርፃ ቅርፅ እና  ቀለም ቅብን ጨምሮ በተለያዩ ሥራዎቿ አንቱታን አትርፋለች፡፡

አርቲስቷ ህብረ ቀለማትን በማዋሃድ ታሪክን እና ባህልን መነሻ ባደረጉ ሥዕሎቿ አማካይነት ዓለም አቀፋዊ እውቅናን አግኝታለች፡፡ አርቲስቷ ከምትሰራቸው ቅርጻ ቅርጾችና ስዕሎች መካከል የሚያምሩ ግን እንግዳ የሆኑ የሴት አምሳያ ቅርጻ ቅርጾች ይገኙበታል። እነዚህን የሥነ ጥበብ ስራዎቿ በጥቁር ማንነት እና ሴትነት ላይ ያተኮሩ ናቸው። በእነዚህ የሥነ ጥበብ ስራዎቿ ድንበር ተሻጋሪ ማንነትን፣ ዘመናዊው የአፍሪካ ማንነትን፣ በተለይ በዘመነ- ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) እያጋጠሙ ስላሉ ውስብስብ በስራዎቿ በስፋት አንጸባርቃለች፡፡ ከዚህ አንጻር ዋንጌቺ ሙቱ አፍሪካዊ ማንነትን በስራዎቿ አጉልታ በማሳየት ዕውቅናን ያተረፈች አርቲስት ለመሆን በቅታለች፡፡

በርተሌሚ ቶጉኦ

እ.ኤ.አ. በ1967 በምባልማዮ በሚባል አካባቢ ካሜሩን ውስጥ የተወለደው በርተሌሚ ቶጉኦ አፍሪካዊ ማንነትን በስራዎቹ አጉልቶ በማሳየት የሚታወቅ አርቲስት ነው፡፡ አርት ፎረም የተሰኘ ገጸ- ድር በፈረንጆቹ 2020 ባስነበበው ጽሑፍ ቶጉኦ ቅርጻ ቅርጽን፣ ስዕልን እና ፎቶ ግራፍን መነሻ በማድረግ የሚከይን አርቲስት ነው፡፡ በሥነ ጥበብ ስራዎቹ የአፍሪካውያንን ማንነት፣ የስደት እና ተያያዥ የሆኑ ችግሮች አጉልቶ በማሳየት ይታወቃል፡፡ ቶጉኦ በተለይ ተወልዶ ያደገባት ሀገሩ ካሜሮንና አፍሪካዊ ማንነቱ የጥበብ ስራዎቹ እምብርት ናቸው፡፡ ቶጉኦ ሰውን ከተፈጥሮ ጋር በሚያስተሳስሩና የሥነ- ምህዳር ጉዳዮችን በሥነ ጥበብ ስራዎቹ ላይ አፅንዖት ይሰጣል።

አርቲስቱ ከሥነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎቹ ባሻገር በመኖሪያ ቤቱ ካሜሩን ውስጥ በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ዘመናዊ ጥበብን እና ባህልን ለማስተዋወቅ እ.ኤ.አ. በ2008 “Bandjoun Station” የተሰኘ ተቋም በመመስረትም ይታወቃል። በዚህ የሥነ ጥበብ ተቋም ውስጥ የስዕል ኤግዚቢሽን ይታያል፤ ወጣቶች አፍሪካዊ ማንነትን እና ዕሴቶችን እንዲያውቁ ለማስቻል መጽሐፎችን የሚያነቡበት ቤተ መጻሕፍትና የአካባቢው ሰው እረፍት እያደረገ የሚዝናናበት የአትክልት ስፍራ ሰርቷል፡፡ ከዚህ አንጻር አርቲስቱ ከሥነ ጥበብ ስራዎቹ ባሻገር የማህበረሰቡን አዕምሮ በሚያበለጽግ ተግባር ላይ በመሳተፍም ጭምር አንቱታን አትርፏል።

እስክንድር ቦጎስያን

ኢትዮጵያዊው ሰዓሊ እስክንድር ቦጎስያን አፍሪካዊ ማንነትን እና ዕሴትን በጥበብ ስራዎቹ ውስጥ አጉልቶ በማሳየት የሚታወቅ ከያኒ ነው። እስክንድር ውብና በህብረ ቀለማት ያጌጡ ስዕሎችን በመስራት ይበልጥ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀለማትን፣ መስመሮችንና ቅርጾችን አደብዝዞ መስራት እስክንድር የሚታወቅበት ሌላኛው የኪነት መልኩ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ደብዛዛና ፍዝ የሚመስሉ የአርቲስቱን ስዕሎች በብርሃን እገዛ ሲታዩ እጅግ አብረቅራቂና በህብረ ቀለማት የተሽቆጠቆጠ ውበትን የሚያፋልጉ እንዲሁም የደበዘዙ አፍሪካዊ ዕሴቶችን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ 

ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ ‘Modernist Art In Ethiopia’ በተሰኘው መጽሐፏ እንዳሰፈረችው በእስክንድር ስዕሎች ላይ የምናያቸው ደብዛዛ የሚመስሉ ስዕሎች በብርሃን ዕገዛ ሲታዩ ግን አብረቅራቂ ውበትን ይፈነጥቃሉ። የዚህ ውክልና (representation) በቅኝ ገዢዎች እንዲጠለሽ የተደረገውን የአፍሪካውያን ማንነትና እሴት ከስር መሰረቱ ፈልገን ስናወጣው ያለውን ከፍተኛ ዕምቅ አቅምና ውበት ለመግለጽ እንደሆነ አስፍራለች፡፡ እስክንድር በሌሎች ኪነ ጥበባዊ ስራዎቹም ላይ አፍሪካዊ እሴቶችን እና ትውፊቶችን የሚያጎሉ የፈጠራ ስራዎች በመስራት የሚታወቅ ታላቅ ከያኒ ነው፡፡

ከላይ ያነሳናቸውን በማሳያነት ጠቀስን እንጂ ያዴሳ ቦጂያን ጨምሮ ለአፍሪካዊነት አይተኬ ሚና የተጫወቱ ከያኒያን እንዳሉ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review