አፍሪካውያን በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የጋራ ድጋፍ እንዲያደርጉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ(ኢ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
በአፍሪካ ህብረት የድጋፍና የማረጋጋት ተልዕኮ በሶማሊያ (AUSSOM) ስር ወታደሮች ያዋጡ ሀገራት(TCCs) አስቸኳይ የመሪዎች የጋራ ጉባኤ ዛሬ በዩጋንዳ ተካሄዷል።
ጉባኤው በዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ በተደረገ ግብዣ የተካሄደ ነው።
በጉባኤው ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ ተሳትፈዋል።
በመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባኤው ተሳትፏል።
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነም ተሳታፊ ሆነዋል።
ጉባኤው በዋነኛነት አዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮን በማጠናከር፣ በሶማሊያ እና በቀጣናው የተጋረጠውን የሽብርተኝነት የማንሰራራት ሁኔታን በመመከት ላይ ያተኮረ መሆኑን በካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ጉባኤው ከሚያዚያ 14 ጀምሮ ወታደራዊ ሲኒየር ኦፊሻሎችና የቋሚ ፀሐፊዎች፣ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዷል።
አስቸኳይ የመሪዎች የጋራ ጉባኤው ላለፉት ሶስት ቀናት በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ መክሯል።
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) ባደረጉት ንግግር የሶማሊያ መንግስት እስከ አሁን የሄደበት መንገድ አድናቆት የሚሰጠው ቢሆንም፣ የፀጥታ ተቋማትን የማጠናከርና የማቀናጀት ስራ ላይ አበክሮ መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የሶማሊያ የጸጥታ ኃይል በራሱ አቅም ግዳጆችን የመወጣት አቅም ላይ እስኪደርስ ድረስ ድጋፏን ማድረግ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ፋይናንስን በተመለከተም አሁንም ከነባርና አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮች ድጋፍ ለማግኘት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ህብረት እስከ አሁን ከህብረቱ ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ክምችት ላይ አውሶምን ለመደገፍ የሄደበትን መንገድም አድንቀዋል።
አፍሪካውያን በሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በፓን አፍሪካኒዝም እና በአፍሪካ አንድነት የጋራ መንፈስ የሶማሊያን መንግስት እንዲያግዙ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች ብለዋል።
በአውሶም ጥላ ስር ወታደር ያዋጡ ሀገሮች በበኩላቸው በቀጣይ የአልሸባብን በአዲስ መልክ የመደራጀት እንቅስቃሴ ለመግታት በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የኤምባሲው መረጃ ያሳያል።