አፍሪካ እንዴት የምግብ ዋስትናዋን ታረጋግጥ?

You are currently viewing አፍሪካ እንዴት የምግብ ዋስትናዋን ታረጋግጥ?

ከዓለም ሁለተኛ ትልቅ አህጉር የሆነችው አፍሪካ በበርካታ አስገራሚ ተቃርኖ የተሞላች ስለመሆኗ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የፓን አፍሪካ ባንክ እ.ኤ.አ በ2024 ያወጣው መረጃ አህጉሪቱ ከጠቅላላ የቆዳ ስፋቷ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ 65 በመቶ አላት ይላል፡፡ ይህን ሀብቷን በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል ብትችል እ.ኤ.አ በ2050 ዘጠኝ ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ የሚገመተውን የዓለም ሕዝብ መቀለብ የሚያስችል እምቅ አቅም እንደሆነ ያትታል፡፡ ይሁንና በተቃራኒው አሁን ላይ አህጉሪቱ ከዓለም አቀፍ የግብርና ምርት ያላት ድርሻ ከ10 በመቶ የዘለለ አይደለም።

የዩ.ኤን.ዲ.ፒ መረጃ እንደሚያሳየውም፣ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት በአፍሪካ የረዥም ጊዜ ፈተናዎች አንዱ ሆኖ ቀጥሏል። ይሁንና የአህጉሪቱ ትልቅ ተቋም በሆነው የአፍሪካ ህብረት ጥላ የተሰባሰቡት የአፍሪካ ሀገራት ይህንን ችግር ከስሩ ነቅሎ ይጥልልናል ያሉትን ሰባት ዋና ዋና ዒላማዎችንና 20 ግቦችን በውስጡ የያዘው ‘አጀንዳ 2063’ን ቀርጸው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

‘አጀንዳ 2063’ የተሰኘው እቅድ ከሁሉም በላይ በአህጉሪቱ ላይ የሚቃጡ ጦርነቶች ማስቆም፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ማዘመንና ሌሎች መሰረታዊ ግቦችን ያካተተ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2025 የተመጣጠነ ምግብ የማይመገበውን አፍሪካዊ ቁጥር ወደ 12 በመቶ ገደማ ማውረድና  “በ2025 ረሃብን እና የምግብ እጦትን ማስወገድ የሚለው ደግሞ ሌላኛው ወሳኝ ግብ ሲሆን፣ እንደ አፍሪካ ህብረት ሪፖርት ከሆነ ደግሞ ይሄኛው የ‘አጀንዳ 2063‘ ግብ እስከ አሁን ባለው ጊዜ በሚፈለገው የውጤት ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ ለመሆኑ በዚህ ረገድ ታቅዶ የነበረው ምንድነው? ለምንስ በበቂ ደረጃ ሳይሳከ ቀረ? የትኞቹስ ሀገራት ለዚህኛው ግብ ስኬት ጥረት አደረጉ? በቀጣይ ግቡን ለማሳካት ምን ማድረግ ታስቧል? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን መፈተሽ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ነው፡፡

አፍሪካ ስለምን የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ ተሳናት የሚለውን ጉዳይ ወደመፈተሹ ከመግባታችን አስቀድሞ የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ የሚባለው መቼ ነው? የሚለውን ነጥብ ማንሳት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ለዚህም የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅትን (ፋኦ) ለጉዳዩ የሰጠውን ፍቺ እናቅርብ። ድርጅቱ እንደሚለው በአንድ ሀገር የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ የሚባለው አብዛኛው ሕዝብ በቂ፣ ጤናማና የተመጣጠነ ምግብ በአስተማማኝ ሁኔታ ማግኘት ሲችልና በየዕለቱ ከ2 ሺህ 100 በላይ የካሎሪ መጠን ሲያገኝ ነው። የምግብ ዋስትና ስለመረጋገጡ ሌላው መመዘኛ  ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት የሚጋለጠው ሕዝብ ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ ከአምስት በመቶ በታች ሲሆን ነው ይላል።

“በ2025 ረሃብን እና የምግብ እጦትን የማስወገድ ጉዳይ አንገብጋቢ የሆነበትና ከ’አጀንዳ 2063‘ ዋነኛ ግቦች መካከል አንዱ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሆን ዘንድ አንዳንድ የአህጉሪቱን መራር ሀቆች ወደማቅረቡ እንለፍ፡፡ በእርግጥ ይህ አሃዝ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ያለማቋረጥ እየቀነስ ቢመጣም በአፍሪካ ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ ለርሃብ የተጋለጠ ነው። ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ አጠቃላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው አፍሪካውያን ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን እ.ኤ.አ በ 2020 ብቻ 282 ሚሊዮን አፍሪካውያን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ገጥሟቸው ነበር፡፡ ይህም ከአጠቃላይ የአፍሪካ ህዝብ ወደ 21 በመቶ የሚጠጋ ነው፡፡

ዕቅዱ ከጸደቀበት ጊዜ አንስቶ በቀጣይ 50 ዓመት የአፍሪካን ዕጣ ፈንታ ይበይናል የተባለለት የ’አጀንዳ 2063‘ እና የምግብ ዋስትና ጉዳይ ያቆራኛቸውም እንደዚህ አይነቶቹ የአፍሪካ መራር ሀቆች ሲሆኑ ይሁንና ከዚህ አንጻር ተይዞ የነበረው ግብ ግን ጊዜ በገፋ ቁጥር መልካም ዜና የተሰማበት አልሆነም፡፡ እ.ኤ.አ 2025 አፍሪካን ከምግብ እጥረት እና ረሃብ ነጻ ለማድረግ በ‘አጀንዳ 2063‘ የተያዘ ቢሆንም በበቂ ደረጃ መሳካት ሳይችል ቀርቷል፡፡ 

በሌላም በኩል የአፍሪካ ችግሮች በአብዛኛው ደካማ የፖለቲካ ውሳኔዎች ውጤቶች እንደሆኑ የሚገልጹት ኮሚሽነሩ በተለይም ለግብርናው ዘርፍ የሚመደበው በጀት አናሳ መሆኑን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። በምግብ ደረጃ የተቀመጠው ቢያንስ 10 በመቶ ቢሆንም አብዛኞቹ ሀገራት በአማካይ 3 ነጥብ 8 በመቶ በጀታቸውን ለግብርናው ዘርፍ ሲመድቡ አንዳንዶቹ 1 በመቶ ድረስ የወረደ በጀት እንደሚመድቡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህም ላይ አህጉሪቱ ኋላ ቀር የሆነው የአስተራረስና የግብዓት አጠቃቀም ዘዴን የሙጥኝ ብላ መቆየቷ ሲጨመርበት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡ ጉዳይ የሰማይ ያህል ርቆ ቆይቷል፡፡

ይህም ሲባል ግን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ተስፋ አስቆራጭና ለግቡ መሳካት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩና ውጤት ያመጡ የአፍሪካ ሀገራት የሉም ማለት አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ለዚህ ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጋና፣ ማሊና ማላዊን የመሳሰሉ ሀገራት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት የተሻለ ዓመታዊ የግብርና ዕድገት ያስመዘገቡ መሆናቸውንም ዓመታዊ የዓለም ምግብ ፖሊሲ ሪፖርት አስፍሯል። እንደዚሁም በግብርና መስክ ያስመዘግቡ ዘንድ ይጠበቅባቸው ከነበረው ከስድስት በመቶ ባሻገር፣ ለግብርና ዘርፍ የመደቡት የመንግሥት ወጪያቸውም በአማካይ እስከ 7 ነጥብ 7 በመቶ ሊያድግ መቻሉም ተረጋግጧል፡፡

እዚህ ጋር ኢትዮጵያን በምሳሌነት መጥቀስ ተገቢ ስለሚሆን ወደዚያው እንለፍ፡፡  ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት “የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነት” ባለችው የግብርናው ላይ እየሰራች ያለው ስራ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡  ከእነዚህ ጥረቶች መካከል ለማዳበሪያና ለምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ለኩታ ገጠም እርሻ፣ ለመካናይዜሽን አገልግሎት ወዘተ መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት ይጠቀሳል። ከዚህ አንፃር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስንዴ ልማት ላይ እየታየ ያለው የምርትና ምርታማነት እመርታ ይበል የሚያሰኝ ነው። ስንዴ በመኸር ብቻ ሳይሆን፣ በበጋ መስኖም እንዲለማ በማድረግ ውጤት ማምጣት እየተቻለ ነው። በተለይም የበጋ ስንዴ ልማት ሥራዎች ከተጀመሩ ጥቂት ዓመታት ወዲህ በመስኖ አምራች ያልነበሩ አካባቢዎች ወደ ስንዴ ምርት እንዲገቡ ተደርጎ አመርቂ ውጤት መታየቱን የግብርና ሚኒስቴር ሪፖርት ያመላክታል።

ከአንድ ወር በፊት በዩጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) ስብስባ ላይ ኢትዮጵያ ፕሮግራሙን ግቦች የሚያሳኩ የተለያዩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች እየተገበረች እንደምትገኝ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል። አክለውም፣ በብሔራዊ ስንዴ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት ኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ምርቷ ወደ 23 ሚሊዮን ቶን ማደጉንና ይህም ሀገሪቱን ለ50 ዓመታት ስታስገባ የቆየችውን ስንዴ በራሷ አቅም እንድታመርት አስችሏታል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ አንገብጋቢ የሆነውን የምግብ ዋስትናን እና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን በመግለጽ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ሀገራት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ናይጄሪያዊው የአቅም ግንባታ ባለሙያና የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው ሳዲቅ ኦስቲን (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡ በተለይም መንግሥታዊ መዋቅሮችን ማስተካከል፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን እና ቃልን ወደ ተግባር ለመለወጥ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የምግብ ዋስትና ዋና ጸር የሆነውን ግጭትን ለማስወገድ የአፍሪካ መሪዎች በትጋት መወጣት ያለባቸው የቤት ስራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኡጋንዳ ካምፓላ የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የድህረ ማላቦ አጠቃላይ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም (ሲ.ኤ.ኤ.ዲ.ፒ) የ10 ዓመት ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር የአፍሪካ ህብረት ባካሄደው ውይይትም የቀጣይ 10 ዓመት ስትራቴጂ አስቀምጧል፡፡ በዚህም በ2035 አህጉሪቱ የግብርና ምርትን በ45 በመቶ ለማሳደግ እና የምግብ ስርዓቷን በአስር ዓመታት ውስጥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የነደፈው አዲሱ እቅድ አካል የሆነውን ከ2026 እስከ 2035 ባለው ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ የግብርና ልማት ስትራቴጂ አጽድቋል። በስትራቴጂክ ዘመኑ አፍሪካ ድህረ ምርት ብክነትን 50 በመቶ ለመቀነስ፣ ከአጠቃላይ የግብርና ምርት በሀገር ውስጥ የተመረተ ምግብ ድርሻው 35 በመቶ ማድረስ የሚሉ መሰል ግቦችንም አስቀምጧል፡፡

በአፍሪካ ህብረት የእርሻ፣ የገጠር እና ዘላቂ የከባቢያዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ “አሁን ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ፣ የለውጥ መንገድን የሚገልጽ የለውጥ ፅንሰ-ሀሳብ፣ ተጨባጭ እና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ስልታዊ ዓላማዎችን አስቀምጠናል፤ የአህጉሪቱ መሪዎች ለዚህ ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል”ም ብለዋል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review