ኢራን ምክንያታዊና ሚዛናዊ ነው ያለችውን የኒውክሌር መርሀግብር ዕቅድ እያዘጋጀች ነው

You are currently viewing ኢራን ምክንያታዊና ሚዛናዊ ነው ያለችውን የኒውክሌር መርሀግብር ዕቅድ እያዘጋጀች ነው

AMN ሰኔ 03/2017

አሜሪካ እና ኢራን በቀጣዩ ሀሙስ በኒውክሌር መርሀግብር ዕቅድ ዙሪያ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

ኢራን በአሜሪካ የተዘጋጀው የኒውክሌር መርሀግብር ዕቅድ ቀደም ብሎ እንደደረሳት ገልፃ ዕቅዱ ጉድለቶች እንዳሉት አስታውቃ ነበር፡፡

በአሜሪካ ተዘጋጀ የተባለው ዕቅድ አሻሚ አንቀፆችን የያዘ ከመሆኑም ባሻገር በኢራን ላይ ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ እንዲነሳ የሚያስችል ባለመሆኑ በኢራን በኩል ተቀባይነት አላገኘም፡፡

በመሆኑም ኢራን ምክንያታዊ እና ሚዛናዊ ነው ያለውችውን የኒውክሌር መርሀግብር ዕቅድ እያጠናቀቀች ሲሆን በቅርቡ ይፋ እንደምተደርግም ነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የገለፀችው፡፡

ዕቅዱ ከአሜሪካ ጋር ለሚደረገው የንግግር መድረክ የስምምነት ማዕቀፍ ሆኖ የሚቀርብ ነው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢራን ዩራኒዬምን በ60 በመቶ ታበለጽጋለች፣ ይህ ደግሞ በፈረንጆቹ 2015 የተቀመጠውን የ3 ነጥብ 67 በመቶ ገደብ የጣሰ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ኢራን የአቶሚክ ጦር መሳሪያን ለመታጠቅ ትፈልጋለች ስትል አሜሪካ ደጋግማ ትከሳለች፡፡ በአንፃሩ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዋና ዓላማ ለሠላም ግንባታ ብቻ ነው ስትል መከራከሪያ ስታቀርብ ሰንብታለች፡፡

እንደ አር.ቲ.ኤ ዘገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውዩክሌር ጉዳይ የሚመለከተው ቦርድ አስተዳደር ከሰሞኑ በቬና እያካሄደ ባለው ስብሰባው ኢራን ከአለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ሁሉን አቀፍ ትብብር እንድታደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኢራን ከኤጀንሲው ጋር በትብብር መሥራት እስካልቻለች ድረስ ግን የኒውክሌር መርሀግብሯ ለሠላም ግንባታ ስለመሆኑ እውቅና ለመስጠት እቸገራለሁ ብሏል ቦርዱ፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review