ኢራን በኒውክሌር ተቋማቶቿ ላይ የተሰነዘረባትን የበቦምብ ጥቃት ተከትሎ አሜሪካን አስጠንቅቃለች፡፡
አሜሪካ በኢራን ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ተከትሎ የቴህራን ምላሽ ምን ይሆን የሚለው አጠያያቂ ሆኗል።
ይህ በጦርነት ወሳኝ ወቅት እንደሆ እና በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ለአሜሪካ ደህንነት ጉልህ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችልም ነው የተመላከተው።
በቀጣናው ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች የተሰለፉ ሲሆን፣ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።
በትናንትናው ዕለት በየመን የሚገኘው እና በኢራን እንደሚደገፍ የሚገለጸው የሁቲ ቡድን፣ አሜሪካ በኢራን ወታደራዊ ተሳትፎ የምታደርግ ከሆነ በቀይ ባህር በአሜሪካ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደገና እንደሚጀምር አስጠንቅቋል።
በአሁኑ ሰዓት ኢራን በአካባቢው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ መሠረቶች ላይ የበቀል እርምጃ ትወስዳለች በሚል በእጅጉ መፈራቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በበኩላቸው፣ በቀጣናው በአስቸኳይ ሰላም የማይሰፍን ከሆነ ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚሰነዝሩ አስጠንቅቀዋል፡፡
በኢራን ሰላም ወይም ባለፉት 8 ቀናት ከታዩት የበለጠ አስፈሪ ነገር ይሆናል ሲሉም ነው ትራምፕ ያስጠነቀቁት፡፡
ዛሬ ሌሊት የወሰዱት እርምጃም ፈታኝ እና ከባዱ እንደነበር ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁንም ገና ብዙ የቀሩ ዒላማዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
በአስቸኳይ ሰላም የማይወርድ ከሆነም፣ ወደ ተቀሩት የጥቃት ዒላማዎች በፍጥነት እና በብቃት እንደሚያመሩ አበክረው አስጠንቅቀዋል፡፡
በታምራት ቢሻው