ኢራን እና አሜሪካ በቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ዙሪያ አዲስ ስምምነት ላይ ከደረሱ ማዕቀቡ እንዴት እንደሚነሳ ግልፅ እንድታደርግላት አሜሪካን ጠይቃለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማይል ባጋሃይ የግልጽነትን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው የእገዳውን እውነተኛ ፍጻሜ በተመለከተ ዋስትናዎችን እና እገዳው እንዴት እና በምን አይነት ሁኔታ እንደሚወገድ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠይቀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ አዲስ የስምምነት ሃሳብን ያቀረበች ቢሆንም የስምምነት ሃሳቡ ግልፅነት ይጎድለዋል በሚል በኢራን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ሾልኮ የወጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ እንደሚያመላክተው ኢራን ዩራኒየም ማበልፀጓን ወደ 60 በመቶ የጨመረች ቢሆንም ለከባድ የጦር መሳሪያ ከሚያስፈልገው 90 በመቶ ርቃ ትገኛለች ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።
በግምገማ ላይ ላለው የአሜሪካ የስምምነት ሃሳብ የኢራን ባለስልጣናት አሉታዊ ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጁ እንደሆነም ዘገባዎች አመላክተዋል።
በሊያት ካሳሁን