AMN-መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) እና የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 57ኛው አህጉራዊ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ ልማትና የፕላን ሚኒስትሮች ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
ኢሲኤ እና ፋኦ ከጉባዔው ጎን ለጎን በትብብር ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአፍሪካ የዘላቂ ግብርና እና የግብርና ንግድ ልማት፣ የምግብ እና የስነ ምግብ ዋስትናን ማረገገጥ ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ነው።
የኢሲኤ የፕሮግራም ድጋፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ስምምነቱን ጊዜውን የጠበቀ ሲሉ ገልጸውታል።
ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዘላቂ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና እና የምግብ ስርዓት መገንባት እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።