የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ከሆኑት ሚስተር አምበሮይስ ፋዮሌ ጋር በልማትና ኢንቨስትመንት ትብብር ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አካሂደዋል።
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እድገት ዙሪያ ተጨባጭ አስተዋጽኦ ከማበርከት አኳያ ጉልህ ሚና ያላቸው ዘርፎች በተለይም በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ፣ ውሃ፣ የንጽህና አጠባበቅና እና በሴቶች ስራ ፈጠራ ልማት እየተደረገ ላለው ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ልማትና እድገቷ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥታ እያከናወነቻቸው ባሉ ዘርፎች ላይ ሙሉ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ድጋፉም ለአዲሱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት በገንዘብ ለመደገፍ ያሉ አማራጮችን ማየትን ጭምር እንደሚያጠቃልል በውይይታቸው ገልጸዋል።
ሁለቱም ወገኖች በቀጣይ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንዲሁም የባንኩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት በተለያዩ ዘርፎችና አማራጮች ላይ ለመወያየት መስማማታቸውን ከዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።