
AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያና ጣሊያን በሴቶች፣ ህጻናት እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ በመሆን ከጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ድኤታ ጆርጂዮ ሲሊ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በውይይቱ እንደገለፁት ጣሊያን እና ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መልካም ግንኙነት አላቸው፡፡
ጣልያን የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኗን በማንሳትም፤ በልማት ትብብርና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጣሊያን የምታደርገውን ጠንካራ ተሳትፎም አድንቀዋል።
በተለይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ከተሰጡት ሀላፊነትና ተግባራት አንጻር እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች በመግለፅ በተለይ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶችን እንዲደግፉ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።
ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በመከላከል እና ምላሽ በመስጠት እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች በማስፋት በጋራ ለመስራት ፍላጎት መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡
በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ ህጻናት በአማራጭ የድጋፍና ክብካቤ አማራጮች ለመደገፍ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በመከላከልና መደበኛ የሆነ ፍልሰትን በመደገፍ በውጭ ሀገር ህጋዊ በሆኑ የስራ ስምሪቶች እንዲሰማሩ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ስራ በመደገፍ በጋራ መስራት እንደሚችሉም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከጣልያን ጋር በዘርፉ ያለንን ግንኙነት ማጠናከራችን በተለይም የሴቶችን፣ ህፃናትን፣ የወጣቶችንና ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን አቅም በማጎልበት የስርአተ -ፆታ እኩልነትንና አካታችነትን ውጤታማ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጆርጂዮ ሲሊ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
አክለውም በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር የሁለትዮሽ ስምምነትን ለመፈረም ጣሊያን ዝግጁ መሆኗን መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡