AMN – የካቲት 10/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የበርካታ አገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ አርዓያ የሆነ ተግባር እየፈፀመች መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ገለፀ።
በሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመክረው የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ፣በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ በአፍሪካ ሕብረት እና ኢጋድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
በመድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት በሁሉም መስክ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
በተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የምስራቅ፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የታላላቅ ሀይቆች ቀጣና ዳይሬክተር ማማዱ ዲያም ባልዴ እንዳሉት ኢትዮጵያ የሀገራትን ስደተኞች ተቀብላ በማስተናገድ አርዓያ ሀገር ናት።
ለአብነትም የሱዳንን ውስጣዊ ችግር ተከትሎ ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሱዳን ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ እያደረገች ያለውን በጎ ተግባር አድንቀዋል።
ሱዳናዊያን ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ለስደት መዳረጋቸውን ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ በሀገሪቷ ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አኳያ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።