AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
በ2017 በጀት ዓመት 6 ወራት ሥራ አፈፃፀም ላይ ባተኮረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስበሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል፡፡
በተለይም ለኢኮኖሚው ዕድገት ትልቁን አስተዋፅዖ የሚያበረክተው ግብርና አስደናቂ እምርታ ማምጣቱን ገልፀዋል፡፡
አምና የአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ ሽፋን ከነበረበት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን አስታውቀዋል፡፡
በ2016 የኩታ ገጠም ማሳ ሽፋን 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ላይ 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል፡፡
በተያዘው ዓመትም በመኸር ወቅት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ፣ በበጋ መስኖ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በጥቅሉ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በስንዴ ተሸፍኖ ከሚገኘው 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 300 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራች ሀገር መሆኗን በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡
በለውጡ ማግስት 700 ሚሊዮን ዶላር ብቻ የነበረው የቡና ገቢ በ2016 ትልቅ ለውጥ በማምጣት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ብለዋል፡፡
በተያዘው 2017 በጀት ዓመት 8 ወራት ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ከቡና ምርት መገኘቱን አስታውቀው በቀሪ አራት ወራት ውስጥ ደግሞ በጥቅሉ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በቅባት እህሎች፣ በሩዝ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በሻይ እና በሌሎችም የተሰሩ ሥራዎች አስደናቂ ውጤት ያመጡ መሆናቸውን ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት፡፡
በማሬ ቃጦ