ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት፣ በእናቶች ሞት ቅነሳ፣ በማህበረሰብ ንቅናቄ እና በሌሎች ተግባራት የዘላቂ ልማት ግቦችን እያሳካች እንደምትገኝ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ሚኒስትሮች በተሳተፉበት መድረክ 3ኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2030 ለማሳካት ያስቀመጣቸውን 17ቱን የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የመድረኩ ተሳታፊ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የዘላቂ ልማት ግቦችን በሁሉም የልማት መስኮች በማካተት እመርታዊ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና በርካታ ስራዎችን ማሳካቷን በማንሳት፥ ለአብነትም በኮሪደር ልማትና በጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የህብረተሰቡን ህይወት የሚያሻሽሉ ሰው ተኮር ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ብቻ በፅዱ ኢትዮጵያ ከ250 በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ የጋራ መጸዳጃ ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ የወንዝ ዳርቻ ልማቱም ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በተናበበ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ማህበረሰቡን በማሳተፍ 25 ቢሊዮን ብር ተሰብስቦ ከ39ሺህ ያላነሱ ቤቶችን በመገንባት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና ለአቅመ ደካሞች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማቱ ያረጁና ለኑሮ የማይመቹ መንደሮችን ወደ ዘመናዊ የክትመት ምዕራፍ በማሸጋገር ለነዋሪዎች ምቹና ዘመናዊ የመኖሪያ ከባቢ መፈጠሩን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የልማት ግቦችን ከማሳካት አኳያ በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ ጭምር የሚጨበጥ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

ሀገራዊ የማምረት፣ የገቢ አሰባሰብ፣ የማልማት እና ህብረተሰብን የማነቃነቅ አቅምን በማሳደግ ጥራት ያላቸው የልማት ስራዎችንና አገልግሎቶችን በአካታችነት ተደራሽ ማድረግ ችለናል ነው ያሉት።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በሀገር አቀፍ የእናቶችን ሞት በመቀነስ በኩል የተመዘገቡ ስኬቶች መኖራቸውን ሶማሌ ክልልን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ በ17 የጠረፍ ወረዳዎች ላይ የእናቶች የጤና አገልግሎትን በማጠናከር ከዚህ ቀደም በወሊድ ምክንያት ይከሰት የነበረውን የእናቶች ሞት አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ሚኒስትሮችም የዘላቂ የልማት ግቦችን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ከተቀመጡ ሀገራዊ ግቦች ጋር በማጣመር እየተተገበሩ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፥ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ባለፉት ዓመታት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከፍተኛ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከዘላቂ የልማት ግብ አንጻር በተለይ በሁሉም የልማት መስኮች የስራ ዕድል ፈጠራን በማስፋት በየዓመቱ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቷን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ደግሞ ዲጂታል የስራ ገበያ ስርዓት መዘርጋቱን ነው ያነሱት።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም አሁን 17 በመቶ መሆኑን በማንሳት፥ ኢትዮጵያ ግን 63 በመቶ በማሳካት ከፍተኛ ስራ መስራቷን ተናግረዋል።
የድህነት ቅነሳ፣ የከተሞች ዘላቂ ልማት፣ የትምህርት፣ የጤና እና መሰል ስራዎች በፈቃደኝነት የግምገማ ሪፖርቱ ላይ ብቻ ሳይሆኑ በሌሎች ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ጭምር ተካትተው ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በተሞክሮነት እየቀረቡ ነው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት ማጠቃለያ፥ በ3ኛው የዘላቂ ልማት ግብ የፈቃደኝነት ግምገማ ሪፖርቱ የቀረቡ አመላካቾች ተስፋ ሰጪ ሀገራዊ አፈጻጸም መኖሩን እንደሚያሳዩ ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በድህነት ቅነሳ የህብረተሰቡን ኑሮ በማሻሻል እና አካታች ልማትን በማረጋገጥ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።
እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶችም ቀሪ ስራዎችን በስትራቴጂዎቻችን እያካተትን ይበልጥ ተግተን እንድንሰራ የሚያነሳሱ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
ለግቦቹ መሳካትም ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ የሀብት ማሰባሰብ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፥ የዘላቂ ልማት ግቦችን ዕቅድና አፈጻጸም በሚለካ መልኩ መሰነድ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።