ኢትዮጵያ በኢስዋቲኒ እየተካሄደ በሚገኘው በ3ኛው የኮፊ አናን የመንገድ ደህንነት ሽልማት መድረክ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን የተመራ የልኡካን ቡድን በሽልማት መድረኩ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትን ለማስፈን ያደረገቻቸው ጥረቶች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ለዚህ ጥረትም ዕውቅና የሚሰጣት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
የኮፊ አናን የመንገድ ደህንነት ሽልማት በአፍሪካ ጎዳናዎች ላይ ህይወትን ለማዳን የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሀገራትና ባለድርሻ አካላትን እውቅና ለመስጠት የሚዘጋጅ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
የአሁኑ 3ኛው የሽልማት መድረክ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንገድ ደህንነት ልዩ መልዕክተኛ ዣን ቶድት እና የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን የአፍሪካ ህብረት ምክትል ዳይሬክተር አንቶኒ ፔድሮ በተገኙበት በኢስዋቲኒ እየተካሄደ ይገኛል፡፡