AMN – የካቲት 25/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለጥራት በሰጠችው ከፍ ያለ ትኩረት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጥራት መንደር መገንባቷ ጥቅሙ ለመላው አፍሪካዊያን መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የደረጃዎች ድርጅት ፕሬዝዳንትና የጋና የስታንዳርድ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከፕሮፌሰር አሌክስ ዶዶ ጋር በሁለቱ ሃገራት ጥራትን ለማላቅ እና በትብብር በሚሰሩ ስራዎች ላይ ገንቢ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር አሌክስ ዶዶ በጥራት መንደር ጉብኝታቸው፣ ባዩት መልካም ተግባር መደነቃቸውንና ለአፍሪካዊያን ከፍታ ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን መግለፃቸውም ተመላክቷል፡፡
በዚህ የጥራት መንደር ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ባለሙያዎችን በስልጠና ለማብቃት የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኗን እንደገለጹላቸው ያመላከቱት ሚኒስትሩ፣ ጋናዊያን የዘርፉ ባለሙያዎችም መጥው እንዲሰለጥኑ መጋበዛቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱ ሃገራት የአፍሪካን አንድነት ለማጽናት እንደተባበሩ ሁሉ የአፍሪካን የጥራት ልክ ለማላቅም በትብብር መንፈስ መስራት ወሳኝ መሆኑን የጋራ ግንዛቤ ላይ እንደደረሱ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡