AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ብራዚል በግብርና እና የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ፥ ከብራዚል የማህበራዊ እድገት፣የቤተሰብ ድጋፍ እና የድህነት ቅነሳ ሚኒስትር ዌሊንግተን ዲያስ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ብራዚል በግብርና እና የምግብ ዋስትና መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
አምባሳደሩ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ግብርናን የማዘመን፣ የምግብ ሉዓላዊነት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ እና በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የተከናወኑ በርካታ ስራዎች እና የተመዘገቡ ውጤቶችን አስመልክቶ ለሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዌሊንግተን ዲያስ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ የተገኙ ውጤቶች ትምህርት የሚወሰድበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ብራዚል ድህነትን በመቀነስ እና ረሃብን በመዋጋት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸው፥ በድህነት ቅነሳ እና ረሃብን በመዋጋት በሚደረጉ ተግባራት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እና በቅርበት እንሰራለን ብለዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው በግብርና እና በምግብ ዋስትና መስክ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።