ኢትዮጵያ እና አውስትራሊያ የሁለትዮሽ እና የባለብዝሃ ወገን ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

AMN-ህዳር 2/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እና አውስትራሊያ የሁለትዮሽ አጋርነታቸውንና በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌትን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እና በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ማስፋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ለረጅም ጊዜያት የቆየ ትስስር በዲፕሎማሲ ስራው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አመልክተዋል።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን ባማከለ መልኩ ኢኮኖሚ እና አቪዬሽንን ጨምሮ በሌሎች ቁልፍ መስኮች ትብብራቸውን ለማሳለጥ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት በግብርና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በምግብ ዋስትና፣ በትምህርት እና በስርዓተ ጾታ እኩልነት ላይ ያስመዘገቧቸውን የትብብር ስኬቶች አድንቀዋል።

የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር አድማስ ማስፋት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ እና አውስትራሊያ የሁለትዮሽ አጋርነታቸውንና በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review