በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በተካሄደው 4ተኛው የኢትዮ-ኡጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ በአጭር ፊርማ ደረጃ ፈርመውት የነበረውን የአየር አገልግሎት ስምምነት በሙሉ ፊርማ አጠናቀዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው የበረራ አገልግሎት ስምምነት በበረራ ምልልስ፣ መዳረሻ ከተሞች፣ የትራፊክ መብት፣ የአየር መንገዶች ውክልና እና ለበረራ ጥቅም ላይ የሚውሉ አውሮፕላኖች ላይ የነበሩ ገደቦችን ያነሳና ተወካይ አየር መንገዶች በሁለቱ ሀገራት መካከል እና በአፍሪካ ሰማይ ላይ በሙሉ ነፃነት መብረር የሚያስችላቸው ነው፡፡
ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የፈረሙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዴይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ሲሆኑ፣ በኡጋንዳ በኩል ደግሞ የሀገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስትር ቢያሙካማ ፍሬድ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።