በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በ2025 የዓለም ባንክና የአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት የፀደይ ስብሰባዎች ወቅት ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴቭ ጃጋድሳን ጋር ተወያይቷል።
በስብሰባውም ላይ ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በተተገበሩ ማሻሻያዎችና በተወሰዱ እርምጃዎች እንዲሁም በቅርቡ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት በተደረገው የችርቻሮና የፋይናንስ ዘርፍ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈጻሚውም የልማት እና ፋይናንስ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ትኩረት አድርጎ በሚሰራባቸው ዘርፎች ማለትም የአይሲቲ፣ የማዕድን፣ የመሰረተ ልማትና ግብርና ዙሪያ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ በተጠቀሱት ዘርፎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመመለከት ፍላጎት እንዳለው አመላክተዋል።
ሚኒስትሩም በበኩላቸው፤ ሥራ አስፈጻሚው በጠቀሱዋቸው ዘርፎች በርካታ የኢንቨስትመንት እድሎች ያሉ መሆኑንና የልማት እና ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ልኡክ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አዲስ የታቀደውን የአለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ፋይናንስ ለማድረግ የሚችልባቸው እድሎች ካሉ እንዲሁም ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮችንም እንዲመለከት ጋብዘዋል።
ሁለቱ ወገኖች በቀረበው ሃሳብ መሰረት በመጪው ወራቶች በሚደረግ ይፋዊ ጉብኝት ወቅት በሚኖሩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ቀጣይ ውይይት ለማድረግ መስማማታቸውን ከአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡