AMN – መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የላቲን ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር በአምባሳደር ሄሌና ኤራክሲነን ከተመራ የፊንላንድ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያና ፊንላንድ በውሃው ዘርፍ በሚያደርጉት ትብብር ላይ ትኩረት አድርጎ የተካሄደ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የፊንላንድ መንግስትና ህዝብ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀው፤ የፊንላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር የሚተገብረው አምስተኛው ዙር የኮዋሽ ፕሮግራም ሊያካሂዳቸው የሚገቡ ማሻሻያዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ውሃ አጠርና ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ፤ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው የመጠጥ ውሃ መሰረተ ልማቶች የሚገኙበት አካባቢዎች ላይ፤ በፀሀይ ሀይል የሚሰራ የውሃ መሰረተ ልማት መገንባት ላይ፤ የውሃ አገልግሎቶችና የዋሽ ኮሚቴዎች ፤ የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይና የውሃ ሀብት መረጃ ስርዓት ማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት በሚያስችል መልኩ መተግበር እንደሚገባው ገልጸዋል።
በፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ የመካለኛው ምስራቅና የላቲን ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሄሌና ኤራክሲነን በበኩላቸው አምስተኛውን ዙር የኮዋሽ ፕሮግራም አተገባበርን በተመለከተ በቀጣይ ውይይቶችን በማድረግ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ ማስረዳታቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።