‎ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ኢኮኖሚ ኢ-ተገማች የሆነውን የዓለም ሁኔታ ያገናዘበ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን

You are currently viewing ‎ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ኢኮኖሚ ኢ-ተገማች የሆነውን የዓለም ሁኔታ ያገናዘበ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን

AMN – ጥር 9/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ኢኮኖሚ ኢ-ተገማች የሆነውን የዓለም ሁኔታ ያገናዘበ፣ ነባር አቅሞችን በማጠናከር ወደ አዳዲስ ዘርፎች የሚያሻግር፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያበረታታ እና የሚያጠናክር እንዲሁም ወደ መጪው ዘመን የፈጠራ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያስፈነጥር ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለውን ኢኮኖሚ በተመለከተ ባደረጉት ገለፃ፣ የተቃና የኢኮኖሚ ማዕቀፍ በመገንባት ለግብርናው፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለቱሪዝም፣ ለማዕድን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሚዛናዊ ትኩረት የሚሰጥ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ዘላቂ የልማት ፋይናንስ ሥርዓት በመፍጠርም ሀገሪቱን ከብድር ጫና የሚያላቅቅ ስለመሆኑ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህ እውን እንዲሆንም በቅርቡ ለረጅም ጊዜ የቆዩ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ዕድገትን ለማስፈን ሀገሪቱ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷን አስታውሰዋል፡፡

ማሻሻያውም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ የሁለተኛው መካከለኛ ዘመን መርሐ-ግብር ምሶሶ የሆኑትን አራት መሰረታዊ ጉዳዮች የያዘ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እነዚህም፣ በሀገሪቱ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን መፍጠር፣ የንግድ ሥራዎችን የሚያሳልጡ፣ የሚያቃልሉ እና ውጤታማነትን የሚያሻሽሉ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አካባቢዎችን ማሻሻል፣ የሴክተር ሪፎርም በመባል የሚታወቀውን የዘርፎችን ምርታማነት እና ተወዳዳሪነት ማሳደግ እና የመንግስት የማስፈጸም አቅምን ማጎልበት ማዕከል ያደረጉ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ የትኩረት መስክ የብር ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረግ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

ነገር ግን ይህ አንዱ የትኩረት መስክ እንጂ ወሳኙ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የብር የምንዛሪ ተመን በገበያ መወሰኑ፣ አምራቾች አንድን ምርት ለማምረት ከተጠቀሙበት ግብዓት እና ጉልበት ጋር የተመጣጠነ ዋጋ እና ትርፍ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት፡፡

ይህ በበኩሉ የኮንትሮባንድ ንግድን እና መሰል ኢ-መደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የሚገታ ስለመሆኑ ዶክተር ለገሰ አስረድተዋል፡፡

ማሻሻያው ህገ-ወጥ የነበረውን አካሄድ ወደ ህጋዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲቀየር በማድረጉ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ህገ-ወጥነት የገቡ ኃይሎች በህጋዊ መንገድ የሚፈልጉትን ነገር እንዲያገኙ የኢኮኖሚ ሁኔታው ምቹ መደላድል እንደፈጠረላቸው አመላክተዋል፡፡

የብር ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉን ተከትሎ የወርቅ አምራቾች በዓለም አቀፍ የዋጋ ተመን መሠረት ምርታቸውን ስለሚሸጡ፣ ወርቅን በኮንትሮባንድ ከመሸጥ ይልቅ በማዕከላዊ ገበያ ለብሔራዊ ገበያ እንዲሸጡ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህም ብሔራዊ ባንክ በታሪኩ ገዝቶት የማያውቀውን ከፍ ያለ የወርቅ መጠን እየገዛ እንደሚገኝ እና ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኝ እንደረዳው አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ በሌሎች ሸቀጦች በተለይም በቡና፣ በቅባት እህሎች እና ጥራጥሬ እንዲሁም በአምራች ኢንዱስትሪዎች እና በአገልግሎት ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማጎልበት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት እና ክምችት ከፍ እንዲል እረድቷል ብለዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review