AMN – የካቲት 17/2017 ዓ.ም
በቻይና የዓለማቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክርቤት ምክትል ፕሬዝደንት የተመራን ልዑክ ተቀብለው፣ በሁለቱ ሃገራት የንግድ ግንኙነትና ፕሮሞሽን ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረገች መሆኗንና ከቻይና ጋርም በቀጣይ ይህን ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር ማስገንዘባቸውንም አመላክተዋል፡፡
የንግድ ግንኙነቱ ስለሚጠናከርበት ሁኔታም ምክረ ሀሳብ አቅርበናል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ልዑካን ቡድኑ በቆይታቸው ተዘዋውረው በተመለከቱት የለውጥ ውጤቶች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ቻይና በቀጣይ ሐምሌ ወር በምታዘጋጀው 3ኛው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ባቀረበችው ግብዣ መሰረት የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ የቻይናን ገበያ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ዝግጅት ተደርጎ እንደሚሳተፍ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡