ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በጤናው ዘርፍ ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።
በንፅህና እና በሽታ መከላከል ዙርያ ያተኮረ የመጀመርያው የሩሲያ አፍሪካ የስልጠናና የትብብር መድረክ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በጤናው ዘርፍ ያላትን ግንኙነት በማድነቅ በቀጣይ ጊዜያት ይህንን ትብብር እንደምታጠናክር ገልፀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላዲሚር ፑቲንን መልዕክት ያስተላለፉት በሩስያ የፌደራል አገልግሎት ለተጠቃሚዎች መብትና ጥበቃ ቅኝት ሀላፊ ኘሮፌሰር አና ዩ ፖፖቫ፤ በቀጣይ ጊዜያት የትብብር እና የስልጠና ማዕከሎች እንደሚቋቋሙ እና ሩስያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ስትራቴጂክ አጋርነት እንደምታስቀጥል አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ሩሲያ ለኢትዮጵያ 110 ሚሊየን ብር የሚገመት ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ ድጋፍ አድርጋለች።
ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪውን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ለጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስረክበዋል፡፡
ላብራቶሪው ከ600 በላይ በሽታዎችን መመርመር የሚያስችል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ለያዘችው በሽታን ቀድሞ የመከላከል ተግባር ሚናው የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ላብራቶሪው ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎችና ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የሚያገለግል ይሆናልም ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
ለሶስት ቀናት በሚቆየው የስልጠናና የምክክር መድረክ ከ15 የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በሔቨን እያዩ እና ሩዝሊን መሀመድ