ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የጤና ዘርፍ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የጤና ዘርፍ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ
  • Post category:ጤና

AMN ሰኔ 3/2017

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የጤና ዘርፍ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በተገኙበት ከቻይና መንግስት በድጋፍ የተገኘ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ርክክብ ተካሂዷል፡፡

ዶክተር መቅደስ ዳባ በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ቻይና ያደረገችው ድጋፍ ተላላፊና መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን ለመግታት የዓለም አቀፍ ትብብርን አስፈላጊነት ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነቻቸው ባሉ ሥራዎች ቻይና ጠንካራ አጋር መሆኗን ጠቅሰዋል።

የዛሬው ድጋፍ በተለይም የኮሌራ በሽታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ተላላፊና መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን ከአጋር አካላት ጋር በሚደረጉ ትብብሮች፣ በስትራቴጂክ እቅድ እና ቀጣይነት ባላቸው ተግባራት መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው፥ የሁለቱ ሀገራት የጤና ዘርፍ አጋርነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ፣ለረጅም ጊዜ የዘለቀና ጠንካራ መሆኑን አንስተዋል።

ቻይና ለትብብሩ መጠናከር አበክራ ትሰራለች ያሉት አምባሳደሩ፥ በመድሃኒት፣ ክትባትና የህክምና አገልግሎት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፥ ከቻይና የተገኘውን ድጋፍ ክትባቱ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና በህክምና መሳሪያዎችና መድሃነቶች አቅርቦት ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው፥ ከቻይና ጋር በተለያዩ የህብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review