ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት አላት- አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት አላት- አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

AMN – ጥር 9/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

አፈ ጉባኤው በዶ/ር መሐመድ ጋሊባፍ (ዶ/ር) ከሚመራው የፓርላማ ልዑካን ቡድን ጋር በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት በሀገራዊና ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ኢትዮጵያ እና ኢራን ጋር ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ በወዳጅነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ በኢራን ቆንፅላ መክፈቷን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ በማደግ ላይ ያለች እና በርካታ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት ያሉት አፈ-ጉባኤው በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አብረው በመስራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

የኢራኑ አፈ-ጉባኤ ዶ/ር መሐመድ ጋሊባፍ በበኩላቸው፣ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ እና ባህል ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም ሀገራቸው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ እድገት ለማጠናከር በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ አማራጮች በመደገፍ ወዳጅነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስረድተዋል፡፡

አፈ-ጉባኤ መሐመድ ጋሊባፍ (ዶ/ር) ለልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስት እና ፓርላማው ላደረገላቸው አቀባበል ምስጋና ማቅረባቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያሳያል፡፡

በመጨረሻም አፈ ጉባኤዎቹ በምክር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ችግኝ የመትከል ስነስርዓት አካሄደዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review