ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እና ሞንጎሊያ የተቀቀለ ስጋ መላክ መጀመሯ ትልቅ ስኬት ነዉ – አምባሳደር ድሪባ ኩማ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

You are currently viewing ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እና ሞንጎሊያ የተቀቀለ ስጋ መላክ መጀመሯ ትልቅ ስኬት ነዉ – አምባሳደር ድሪባ ኩማ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

AMN – መጋቢት 27/2017

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ካከናወነቻቸው ተግባራት ውስጥ አንዱና ትልቅ ስኬት ነው የተባለለት ወደ ቻይና እና ሞንጎሊያ ጥራቱና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የተቀቀለ ሥጋ መላክ መጀመሯ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከሚሌ ኳራንታይን 400 ሺህ የቁም እንስሳት ጤንነታቸው ተረጋግጦ በባለሥልጣኑ ሰርተፍኬት ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን አመለከቱ፡፡

አምባሳደር ድሪባ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ ባለሥልጣኑ፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወር ግምገማ እንዳመለከተው ከያዛቸው እቅዶች 96 በመቶውን ማሳካት ችሏል።

ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ አንዱና ትልቁ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ጥራቱና እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የተቀቀለ ሥጋወደ ቻይና መላክ መጀመሯ ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተቀቀለ ሥጋ ወደ ቻይና ብቻ ሳይሆን ወደ ሞንጎሊያም መላክ ጀምራለች ብለዋል፡፡

አምባሳደር ድሪባ፣ ትልቁ ስኬት ነው ብለን የምንለው የሥጋ ምርታችን ወደ ቻይና እንዲገባ ማድረግ መቻላችን ነው፡፡ ከዚሁ ከሥጋ ምርት ጋር በተያያዘ የቻይና ኤክስፐርቶች ወደ ሀገራችን መጥተውና ያለውን ሁኔታ አይተው ማስተካከል የሚገባንን ምክረ ሃሳብ ሰጥተውናል ብለዋል፡፡

“እኛ ደግሞ ቻይና በምትፈልገው የሥጋ ንግድ ሥርዓት መሠረት በመቃኘታችን ቻይናውያን ተቀብለው ውል መፈራረም ችለናል፤ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ሥጋ ወደ ቻይና መግባት ጀምሯል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እርሳቸው እንደተናገሩት፤ የተቀቀለ ሥጋ ወደ ቻይና ብቻ ሳይሆን ወደ ሞንጎሊያም መላክ ተጀምሯል፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ የምትልከው ዓረብ ሀገር ብቻ ነው፡፡ ወደ ቻይና መላክ የተጀመረው በዚህ ዓመት ነው ማለታቸዉን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review