ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወትን መለወጥ የሚችል የፈጠራ አቅም እንዳለ አይተናል፡- በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

AMN ህዳር 23/2017 ዓ.ም

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡባዊ ትብብር ድርጅት (OSC) ጋር በመተባበር ከ14 ሀገራት የተወጣጡ 41 ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የሚቀርቡቡት አለምዓቀፍ የቴክኖሎጂ አውደርእይ በሳይንስ ሙዝየም የመክፈቻ ፕሮግራም አካሂዷል።

ዓውደ-ርዕዩ ከተለያዩ አህጉራት ጋር በቴክኖሎጂው ዘርፍ የጠበቀ ትብብር በመፍጠር እውቀትን በመጋራት የመፍጠርና የመጠቀም አቅምን ለማጎልበት ያለመ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ( ዶ/ር ) ሀገራችን ለቴክኖሎጂው የሰጠችውን ትኩረት ስኬታማ ለማድረግ በዘርፉ ላይ አቅም ካላቸው ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራንና ውጤት እያመጣን ስለመሆኑ ይህ ታላቁ አለምዓቀፍ የቴክኖሎጂ ዓውደርዕይ ማሳያችን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወትን መለወጥ የሚችል የፈጠራ እምቅ አቅም እንዳለ በዓይናችን አይተናል ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከውጭ የሚመጡ ሀሳቦችን ማላመድ ብቻ ሳይሆን በራሳችን አውዶች፣ ባህሎች እና ማህበረሰቦች ላይ የተመሰረተ ከችግራችን የተወለዱት፣ በአመለካከታችን የሚመሩ እና ማህበረሰቦቻችንን ትርጉም ባለው መንገድ በዘላቂነት ሊጠቀምበት የሚችል ሁነት መሆኑን ገልፀዋል።

የደቡባዊ ትብብር ድርጅት (OSC) ዋና ጸሃፊው መንሱር ቢን ሙሳላም ለስታርታፕ፣ለፈጠራ ባለሞያዎች እና በአገሮች መካከል የተሻሉ የተግባር ልምድ ልውውጦችን እና የጋራ መማማርን በማበረታታት የቴክኖሎጂ ልማት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዓውደ ርዕይ መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ ፈጣሪዎችን እና ተማሪዎችን የቴክኖሎጂ አቅምን በማጎልብ የአባል ሀገራትን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋፆ ለመፍጠር ያገለግላልም ብለዋል።

በደቡብ ትብብር ድርጅት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ሃላፊ ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) አባል ሀገራት በሀገር በቀል ቴክኖሎጂው ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ የጋራ የሆነ አቅም ለመፍጠር ሰፋፊ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

በደቡብ ትብብር አባል ሀገሮቻችን ውስጥ ሀሳቦችን ለማጣመር እና የቴክኖሎጂ የወደፊት እጣ ፈንታን የምናሳይበት አስደናቂ ተሰጥኦ እና ፈጠራ በማጉላት የሀገር ውስጥ ፈጣሪዎችን ማብቃት ብቻ ሳይሆን የገሃዱ ዓለም ተግዳሮቶችን የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችንም እንፈጥራለን ብለዋል፡፡

ዓውደ ርዕዩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 23/2017ዓ.ም ለህዝብ ክፍት ሆኖ ስለሚቆይ መተው በነፃ እንዲጎበኙና እድሉን እንዲጠቀሙ ሚኒስቴሩ በመረጃው አስታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review