ኢትዮጵያ ዓለም ሁሉ የሚቀናበት የአንድነት፣ የውበት እና የልዩ ልዩ ባህሎች ባለቤት ናት- አቶ ጥላሁን ከበደ

AMN – ህዳር 29/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ዓለም ሁሉ የሚቀናበት የአንድነት፣የውበት እና የልዩ ልዩ ባህሎች እና ወጎች ባለቤት መሆኗን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን ያሉት 19ኛው የብሄር ብሄረሶችና ህዝቦች ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ‹‹ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ሀሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ ሲከበር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ ነው፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ አክለውም፣ ቀኑን ለማክበር ከተለያዩ ክልሎች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላመሩ ታዳሚዎች የጥበብ መፍለቂያ፣ የሰላም እና የመቻቻል ተምሳሌት ወደሆነችው አርባ ምንጭ ከተማ እንኳን ደኅና መጣችሁ ብለዋል፡፡

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 32 የሚሆኑ የተለያዩ ብሄረሰቦች በአንድንትና በፍቅር ተቻችለው የሚኖሩበት ክልል መሆኑንም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

ብልፅግና ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የነበሩባትን በርካታ ውስብስብ ችግሮች ተቋቁማ እና ተሻግራ፣ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተስፋ የሚጣልባት እና በብልፅግና ጎዳና ላይ ያለች ሀገር መሆንዋንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

አብሮነት ሲጠነክር ማህበራዊነትም ይጎለብታል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ነጠላ ትርክትን በማክሰም ለአንድነትና ለብልፅግና ተገቢውን ቦታ ልንሰጥ ይገባልም ብለዋል፡፡

ሁላችንም ለህዝባችን አንድነት መጠናከር፣ ለአብሮነት መጎልበትና ለልዩነት ውበት ከትናንት በተሻለ ወኔና ፍጥነት መትጋት ይጠበቅብናል ሲሉም ገልጸዋል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ጥላሁን ከበደ፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review