AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ( ዶ/ር) ገለጹ፡፡
“Shaping Future Governments” በሚል መሪ ሀሳብ በዱባይ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተለያዩ የጎንዮሽ ምክክሮች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ባለው የአለም መንግስታት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፎዋን አጠናክራ ቀጥላለች።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ ( ዶ/ር) የዘላቂ የልማት ግቦችን አፈጻጸም አስመልክቶ በተካሄደው ምክክር ላይ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
ከቁልፍ የልማት አጋር አገራት እና ከዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ጋር በተደረገው ምክክር ላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ግቦቹን ለማሳካት እያደረገቸው ስላው ጥረት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የልማት አጋር አገራት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው “Reimagining Technology for Government” በተሰኝ ውይይት ላይ ተሳተፎ አድርገዋል፡፡
በውይይቱ መንግስታት ስለ ቴክኖሎጂ ያላቸውን ዕይታ በድጋሚ እንዲያጤኑ የሚጠቁሙ ሞጋች ሃሳቦች ተነስተዉበታል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የቴክኖሎጂ ዘርፉን ማዘመን ለሁለንተናዊ ልማት መሰረት ነው ብሎ እንሚያምን ገልጸው አገሪቱ ፈጠራን ለማሳደግ እየወሰደቻቸው ያሉ ቁልፍ ጅምር ስራዎችን በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን በአቡዳቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡