ኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎትን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ሰፊ የለውጥ ስራቸውን እያከናወነች መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
የመንግስት ተቋማት ተለዋዋጭ ከባቢያዊ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙና የተከማቹ ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን ለመቅረፍ ትኩረት ያደረገው 10ኛ የአፍሪካ ፐብሊክ ሰርቪስ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
ኮንፍረሱ ላይ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉበት ይገኛል።
ኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ ሰፊ የለውጥ ስራ እያከናወነች መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የዚህ ለውጥ ስራ የተግባር ማሳያ ነው ብለዋል።
ኮንፈረንሱ በአፍሪካ የተከማቹ የአገልግሎት አቅርቦት ችግሮች በመፍታት አካታች፣ ዘላቂ ልማት የሚያመጣ፣ ተጠያቂነት የሚያሰፍን፣ የሰብዓዊ መብት የሚያከብር፣ የህዝቦች ትስስር የሚያጠናክር ከባቢያዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያግዙ ጠንካራ ምክክሮች የሚደረግበትም ነው ተብሏል።
በአሰግድ ኪዳነማሪያም