ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር በትክከለኛ የልማት መንገድ ላይ እንደምትገኝ ተመላከተ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር በትክከለኛ የልማት መንገድ ላይ እንደምትገኝ ተመላከተ

AMN- ግንቦት 15/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር በትክከለኛ የልማት መንገድ ላይ እንደምትገኝ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከፌዴራልና ከክልል የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመስኖ ስንዴ ልማትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የልማት ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ የብዝኃ ዘርፍ ልማት አቅጣጫን እየተከተለች መሆኗን አንስተዋል።

ሀገሪቱ በግብርና ምርታማነት በተለይም በስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ጤፍና ሩዝ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝም አስረድተዋል።

የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የሚታረስ መሬትን መጨመር፣ በሄክታር የሚገኝ ምርትን ማሳደግና የምርት ወቅትን በመጨመር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እየተዘመገበ ነው ብለዋል።

በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ በተመዘገበው ስኬት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ከማስቀረት ባለፈ ለውጭ ገበያ ወደ መላክ መሸጋገር ተችሏል ነው ያሉት።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ተዘዋውረው የተመለከቱት የመስኖ ስንዴ ልማት አስደናቂ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

አንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ቀለብ እየተሰፈረላቸው ይኖሩ እንደነበር በማውሳት በአሁኑ ወቅት የአካባቢያቸውን አቅም በመጠቀም ከተረጅነት ተላቀው ለገበያ እስከማቅረብ ደርሰዋል ብለዋል።

በጉብኝታቸው አርሶ አደሩ ሀገር በቀል እውቀቱን ተጠቅሞ ወንዞችን እየገደበ በርካታ ማሳ ማልማት መቻሉን ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል።

ይህም በግብርናው መስክ የተቀመጡ አቅጣጫዎች በስኬታማነት መተግበራቸውን እንደሚያሳይ አንስተዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዓዊነትን ለማረጋገጥ እና ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር ያስቀመጠችው የልማት አቅጣጫ በትክክለኛ መንገድ ላይ ስለመሆኑ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ እምቅ አቅሞችን በመጠቀም ሀገራዊ ግብን ማሳካት እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።

መንግሥት የመስኖ ልማትና የሌማት ትሩፋትን ማጠናከር፣ አገልግሎትን ማሻሻል፣ ምርታማነትን ማሳደግና ዘላቂ ሰላምን መገንባት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን በባለቤትነት ማሳካት እንዳለበት መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review